Total Pageviews

Saturday, April 27, 2013

“Don’t Judge a book by its cover “አሉ ፈረንጆቹ ሙድ ሲይዙብን



“Don’t Judge a book by its cover “አሉ ፈረንጆቹ ሙድ ሲይዙብን
ፍተሻ አለም ላይ
ፍተሻ ለግል ፤ለማህበረሰብ እና ለሀገር ደህንነት ያለው አስተዋፅዎ እጅግ በጣም ከፍተኛ መሆኑን ሁላችንም የምንስማማበት ይመስለኛል፡፡ከደህንነት ጥበቃ ማነስ አንጻርም የስንቱ ህይወት በከንቱ እንደቀረም የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ለዚህም ነው ሀገሮች ከምንም በላይ ለጥበቃቸው ትኩረት ሰጥተውና ዳጎስ ያለ በጀት መድበው የሚንቀሳቀሱት፡፡
ፍተሻ እኛ ሀገር
ስለፍተሻ ጉዳይ ሳስብ በአየር መንገድና በከተማችን በሚገኙ ትላልቅ ሆቴሎች ያለው አስተማማኝ የጥበቃና የፍተሻ ሁኔታ በጣም ያረካኛል፡፡ሁሉም ለራሱ ደህንነት ሲል እኩል የሚፈተሽበት፡፡ ያውም በደስታ በነጻነት፤ ያለፍርሀትና የደህንነት ስጋት ሳያጋጥመን ለመዝናናት፤ለመስራት ብሎም ለመጓጓዝ፡፡ነገር ግን……….ነገር ግን ዐረፍት ነገሩን አፍራሽ ያደርገዋል ተብለን አይደል የተማርነው ፡፡
እና እኔም ነገር ግን ብያለሁነገር ግን በፍተሻ ቦታዎች ላይ( በአንዳንድ ሆቴሎች፤ባንኮች ፤የመዝናኛ ስፍራዎች፤ሲኒማ ቤቶችወዘተ) እየደረሰብን ያለው መገለልና መድሎ ይቁምልን ነው፡፡እንዴ ሰው ባገሩ እንዴት ..እንዲህ አይነት መድሎ ይደርስበታል፡፡ቆይ እኔ ምለው ለሀገር ደህንነት ስጋት መሆን ያለበት ኢትዮጵዊ ነው ወይስ የውጪ ዜጋ(እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው ሁሉም የውጪ ዜጋ የሀገር ስጋት ነው፤ኢትዮጵያዊ ደግሞ የሀገር ስጋት ሊሆን አይችልም የሚል የጅምላ ድምዳሜ ላይ አልደረስኩም)፡፡ ነገር ግን ቀለሙ ነጭ ስለሆነ ብቻ ከስጋትና ከጥርጣሬ ነጻ መሆን አለበት ወይ? እንደኛ ቀለሙ ስለጠቆረ ደግሞ(ያውም በገዛ ሀገሩ) መጠርጠር አለበት ወይ ነው ጥያቄዬ? “ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውምአይደል ተረቱ:: ቆይ እርስ በእርስ ከተጠራጠርን ማን ሊያምነን ነው??? ከሀገሬ ወጣ ስል ለሚያጋጥመኝ የተንዛዛ ፍተሻ አሪፍ መጽናኛ አለችኝ እንዴ የኔው የራሴ ሰዎች እንደዚያ አገላብጠው ከፈተሹኝ ባዕዶቹማ እንዴት አይበረብሩኝ? ብዬ እፅናናለሁ፡፡
ከሁሉም ግን ግርም የሚለው ነገር፡፡በገዛ ሀገራችን አንድ አይነት ቦታ ላይ ነጮቹ ሳይፈተሹ ሲገቡ እኛ አንዳንዴ ስብዕናችንን በሚፈታተን መልኩ የምንበረበረው ነገር ነው፡፡አንዳንዴ ንዴታችሁ ብልጭ ብሎባችሁ ለምን የውጪ ዜጎቹ እንደማይፈተሹ ጥያቄ ካነሳችሁማ በቃ ጭራሽ አትገቡም ልትባሉ ሁሉ ትችላላችሁ፡፡
አንዴ እንዲህ ሆነ…
አንድ ስብሰባ ነገር ነበረችኝ፡፡ቦታው በከተማችን ካሉት ትላልቅ ሆቴሎች በአንዱ ነው፡፡ የኔ ስራ ለውይይቱ መነሻ ሀሳብ የምትሆን ጽሁፍ ቢጤ ማቅረብ ነበር፡፡በወቅቱ ቀጫጫ ቤጤ ነበርኩና ያው እንደሚታወቀው እኛ ሀገር ለመከበርና አንቱታን ለማግኘት ስጋ፤ ቦርጭና አለባበስ ግድ ይላል፡፡ያኔ ጥሩ ለብሻለሁ ስጋና ቦርጭ ግን አልነበረኝም ፡፡ማህበረሰባችን ደግሞ እንደ ፋሲካ በግ ከላይ አይቶ ነው የሚገምትህ ምክንያቱም “Don’t Judge a book by its cover “ የምትለውን አባባል አያርፍማ፡፡
እናም ትንሽ አርፍጄ ነበርና በር ላይ ስቻኮል ለፍተሻ ሁለት የሆቴሉ ጠባቂዎች መኪናችንን ያስቆሙናል፡፡እሺ ብለን አቆምንና መኪናችንን አገላብጠው በረበሯት፡፡ሞተር መፍታት ነው የቀራቸው፡፡ጋራዥ ነው እንዴ እስክንል ድረስ፡፡ይሄም አልከፋንም በጄ ብለን ነበር፡፡እኔም ሾፌሩም ውረዱ ተባልን፡፡ወረድን፡፡እኛንም ልክ እንደመኪናዋ በረበሩን፡፡ ኧረ ሞተር እንዳይፈቱብን ተባብለን ተሳሳቅንም ተሳቀቅንም፡፡
ወዴት ነውየሴቷ ጥበቃ ጥያቄ ነበር
ይቅርታ የኔ እህት ሆቴል መስሎኝወዴት ነው ተብሎ ይጠየቃል እንዴ ..? ትንሽ ጥያቄው አናዶኝ ነበር
ማነሽወዴት እንደሆነ ካልተናገርሽ አትገቢም” …በቁጣና በገልምጫ
ሾፌሩ ትንሽ እንደመናደድ እየቃጣው ስለኔ መናገር ጀመረ
አይመለከትህም እሷ ትናገር…”
ስነ ስርአት….” አለ በንዴት ሾፌሩ
በዚህ መሀል አምስትና ከዛ በላይ የሚሆኑ ፈረንጆችን የጫነች ሚኒ ባስ ያለ ክልከላና ያለ ጠያቂ ሰተት ብላ ገባች….አይኔን ማመን ነው ያቃተኝ፡፡ማንም የተናገራት የለም፡፡ በዚህ ቢበቃ እኮ ጥሩ ነው፡፡ ጀርባቸው ላይ አነስ ያለች መኪና የምትጭነውን ያህል ትልቅ ቦርሳ፤ የስፖርት እንዲሁም የሙዚቃ መሳሪያዎችን ያየዘ ሌላ ቦርሳ የተሸከሙና ተራራ ወጪ የሚመስሉ ሶስት ፈረንጆች ቀጥ ብለው ገቡ፡፡ወዴት ነው? እንዴት ነው?ማናችሁ? ያላቸው ሰው አልነበረም፡፡
ይሄኔ ሾፌሩ መሳደብ ጀመረእኔ በቃ የምናገረው ነገር ግራ ገብቶኝ ቆሜያለሁ፡፡በዚህ መሀል ወንዱ ጥበቃ መጣና ከኛ ጋር ክርክር ጀመረ፡፡
የኔ እመቤት የስብሰባው ሰዓት እረፍዶብኛል እባክሽ በኋላ እንነጋገራለን ..አሁን ልግባበጣም በትግስትና በአክብሮት ነበር የጠየኳት፡፡አሻፈረኝ አለች፡፡
እንድዉም መኪናውን አውጣ ምናምን መባል ተጀመረአሁን እኔም ተናደድኩ……ስብዕናዬን ተፈታተኑኝ፡፡ወንዱ ጥበቃ በመሀል መታወቂያ አለ፡፡
መታወቂያን ለሁለታቸሁም አልሰጥም…”አልኩና ስብሰባውን የሚያስተባብረውን አለቃዬን ከውስጥ በስልክ ደውዬ ጠራሁት ፡፡
አለቃዬ ሲሮጥ መጣ ….ዝንጥ ያለ ሱፍ ለብሷ ፤ቦርጭም ስጋም አለው፡፡እኔ ለራሴ ቀጫጫምንም የሌለኝ፡፡
እሱ መምጣቱን ሲያዩ
ወንዱ ጠባቂበአንዴ አከበረኝ አንቺ ምናመን ሲል እንዳልነበርበቃ አሁን እርሶ ይግቡ በኋላ እንነጋገራለንምናምና ማለት ጀመረ ማማን አቃተኝሳኩበት ፤አፈርኩበት፤ቅድም ፍተሻው ላይ የተሳቀኩት ሳያንስ ለሰውዬው አስተሳሰብ እኔ ተሳቀኩኝ
አልገባም አልኩኝአለቃዬኧረ ሰአት እረፍዷል ..እንግዶች እየጠበቁ ነው ምናምንአለ፡፡
አልገባም….መግባት የምፈልገው በራሴ ነው በአንተ ወይም በእገሌ አይደለም፡፡ሀላፊያቸው ይጠራልኝና እሱን አናግሬ እገባለሁከነሱ ጋር በኋላ እነጋገራለሁ አልኩኝ፡፡
ለማንኛሁም ሀላፊው ተጠራ አናገርኩት ገባሁ ስወጣ ግን እነዛ የጥበቃ ሰራተኞችን ዝም ብዬ ላልፋቸው አልፈለኩም ፤ስነምግባሩም አይፈቅድልኝም፡፡ሃላፊያቸው መጣ ፤ይቅርታ ጠየቀኝ፤እነሱም ተጠሩ ይቅርታ ጠየቁ፡፡ይቅርታቸው ግን አልካሰኝም፡፡አላስደሰተኝም፡፡እነዚህ ጥበቃዎች መማር አለባቸው ብዬ አሰብኩኝ፡፡ይቅርታ የእኔ መቤት ስለደረሰብሽ በደል በነሱ ላይ ግን አስተዳደራዊ እርምጃ እንወስዳለንየሀላፊው ንግግር ነበር፡፡አዎ ግዴታችሁ ነውየኔ መልስ ነበር ፡፡
በሳምንቱ
በደርጅታችን በኩል በነዛ ጥበቃዎች ላይ የተወሰደውን አስተዳደራዊ እርምጃ የሚገልጽ ዳብዳቤ ደረሰን፡፡አሁን ተካስኩ አልኩኝ፡፡ትንሽም ቢሆን ከስህተታቸው የተማሩ ይመስለኛል፡፡
እናም እንዲህ ስል አሰብኩኝ፡፡እስከመቼ ይሆን ሰውን በቁመናው፤በአለባበሱ፤በቦርጩ ፤በውፍረቱና መሰል ከሰው ስብዕና ጋር ምንም ተገአቦት በሌላቸው መስፈርቶች መፈረጅና መመዘን የምንተወው?ይሄ ጉዳይስ ከአፓርታይድ በምን ይተናነሳል፡፡ግርም የሚለው ደግሞ የእኛው አፓርታይድ እየደረሰብን ያለው በራሳችን ዜጎች መሆኑ ነው፡፡የሌሎቹስ በነጮቹ ነበር፡፡እኛ ባዶ እጃችንን ሆነን እንዲህ ስንበረበር በሌላ በኩል ደግሞ ምናልባትም ለደህንነት ስጋት የሆኑ ነገሮች የተሸከመ አንድ ፈረንጅ አንድም ጥያቄ ሳይጠየቅ ሰተት ብሎ ይገባል፡፡አይ የኛ ነገር ግራ እኮ ነው ሁሉ ነገራችን፡፡እነሱ ጋር ለደህንነት ከሆነ በቃ ነጭ፤ ጥቁር ፤አርንጓዴ የለም….በቃ ሁልሽም ትበረበሪያለሽ ወይም አትበረበሪም …አለቀ!!
እንደዉም ፈረንጆቹ የራሳችንን ዜጎች እየበረበርን እነሱን ስናሳልፍቸው ምን እያሉ ሙድ እንደሚይዙብን ታውቃላችሁአዳሜ መስሎሽ ነው፤ምን እንደያዝኩ አላረፍሽም …Don’t Judge a book by its cover” hahaha…. የሚሉን አይመስላችሁም፡፡
እናም እባካችሁ
እነሱ እንዲህ ይላሉ “Please don’t judge a book by its cover”…መጽሀፉን በሽፋኑ አትገምግሙት፡፡ጥሩ ነውም መጥፎ ነውም ለማለት መጀመሪያ አንብባችሁ ተረዱትእንደማለት ይሆን፡፡
ቆዳው ስለነጣ ብቻ አትመኑት በአግባቡ ፈትሹት ስለጠቆርንና ስለቀጨጭን ደሞ ጋራዥ እንደገባ መኪና ሞተር መፍታት እስኪቀራችሁ አትበርብሩን ሀሳባችንንም ሳይቀርእባካችሁ ሚዛናዊ ሁኑ፡፡






kuku. A eb እዚሁ ፌስቡክ ላይ በመጻፍ ይታወቃሉ! በሙያቸው ጠበቃ ሲሆኑ የሚያነሷቸውን ማህራዊ ሃሳቦች የሚተቹበት ገጽ አላቸው….እነሆ አድራሻው!  https://www.facebook.com/kuku.eb ኢሜላቸውን ከፈለጉም እነሆ! kuku.eb@facebook.com

Saturday, April 20, 2013

ትምህርት ቤት አልሄድም ምክንያቱም…



    ዛሬ ወደ ትምህርት ቤታችሁ በምናብ ልመልሳችሁ፡፡ ስንቱን ማስታወስ ይቻላል? ከበር ላይ ያሉት ጥበቃዎች፤ የመማሪያ ክፍሎቻችሁ፤ መምህራን (የምትወዷቸው የምትጠሏቸውንም ሊሆን ይችላል)፤ ቤተ-መፅሐፍት፤ ካፊቴሪያው፤ ሽንት ቤቱ...

"ቁም!" አሉ ፕሮፌሰር…እደግመዋለሁ! አላዝቤም አልጠቀምም፡፡ ሽንት ቤቱ...እዛው እንቆያለን… ሽንት ቤት  እንቆያለን ... እንቆያለን ... እንቆያለን…አፍንጫ መያዝ የተከለከለ ነው! ... እንቆያለን…እንቆያለን…በቃ አሁን ይበቃናል...ኡፍፍፍፍፍፍፍፍፍ…ምነው በረጅም ተነፈሳችሁ?

ትዝታው እራሱ ይጨንቃል አይደል?

የመንግስት ትምህርት ቤቶችን የመፀዳጃ ቤት ችግር ያየ የደረሰበት ያውቃል፡፡ በኛ ሃገር ያውም በመንግስት ትምህርት ቤቶች ፊደል ቆጥሮ ስለመፀዳጃ ቤቶች ጥሩ ትዝታ ያለው ካለ በጆሮዬ ሹክ ይበለኝ… በአደባባይ የምነግራችሁ ይህ ሰው ወይ ሀገር ቤት አልነበረም ወይም ቤተሠቦቹ ከላይኛው መደብ ስለነበሩ እንትን ትምህርት ቤት ይሆናል የተማረው፡፡ ምክንያቱም ይህ ችግር የአብዛኛው አትዮጵያዊ ታሪክ ነው ለማለት እደፍራለሁ፡፡


ስለ ትምህርት ቤቶች እናውራ ብለን የለ?....ስለመፀዳጃ ቤቶቻቸው ነው፡፡ መቼም ስንቶቻችሁ ፊታችሁ ጭፈግግ እንዳለ የምታነቡት ፅሑፍ ይቁጠረው….እኔማ የት አያችኋለሁ?

ዛሬ ላይ ትምህርት ቤቶች በአዲስ አበባ እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ 903 አፀደ ህፃናት 730 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እና 169 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከፍቷል፡፡
የመንግስትም የግልም ማለቴ ነው፡፡

ትኩረቴ 65 በሚሆኑት 2ኛ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ ነው፡፡ እዛ ጉዳይ አለኝ!

ከትምህርት ቤት ቁጥር መብዛት ጋር ቅሬታ ያለን አይመስለኝም ....እኔ በግሌ የለኝም፡፡ ለስንቱ መንገድ አሳጥሯል፡፡

"እያደር ትመጣለች" የተባለችውን ጥራት ግን እየጠበቅንሽ ነው በሏት፡፡
ቀርታም እንደሆን፤የደረሠችበትን የሚያውቅ ካለም ይንገረን፡፡
ትዕግስታችን ተሟጠጠ እኮ...

ለዛሬ ወጋችን መነሻ የሆነች አንድ ልጅ ላስተዋውቃችሁ፡፡ ትዕግስት ትባላለች፡፡..... ሰሞኑን ወደ አንዱ ክልል ከተማ ለስራ ሄጄ ነበር… እግር በጉዞ ብዛት ቢያጥር ኖሮ አንገቴ ጋ ሊደርስ ሲል የሆነ ቦታ አረፍ አልኩ፡፡ ትዕግስትን ተዋወቅኩ፡፡

የድንጋይ ንጣፍ ለሚሠሩ ወጣቶች  ሻይና የተጠበሰ ብስኩት ትሸጣለች፡፡ ቀኑ ሰኞ ነው፡፡ ከብዙ ጨዋታ በኋላ ምነው ከትምህርት ቀረሽ አልኳት፡፡ ጊዜ አልፈጀባትም
"የወር አበባ ላይ ስለሆንኩ ነው" አለች፡፡

አንድ ወዳጄ ‹‹ ቀይ ሽብር ሲፋፋም›› ትለዋለች ይህንን ሰሞን… ልዋሰው ለአሁን ብቻ!

እንደ አብዛኞዎቹ የአዲስ አበባ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የትዕግስት ትምህርት ቤት መፀዳጃም እንኳን እንደዚህ ባለው ‹‹የቀይ ሽብር›› ቀን ይቅርና እንዲሁ በአዘቦቱም ከደጁ አትጣለኝ የሚባልበት ነው፡፡

የትምህርት ቤቶቹ መፀዳጃ ቤቶች የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ፍሳሽ መጣጭ ቦቴዎች ናፍቋቸዋል፡፡

ወለሉ መረገጫ የሚባል ክፍት ቦታ የሌለው….. ግድግዳው በእድፍ የተሞላ ነው፡፡

ቅፍፍ ይላል አይደል? ይደብራል! ግን እውነት ነው፡፡

ይህ የትዕግስት ብቻ ታሪክ አይደለም፡፡ ብዙ ሴቶች በደህና ቀናችሁ ለውሃ ሽንት እንኳ ወደ መፀዳጃ ቤት ላለመሄድ ጉዳያችው ከበር ውጪ ቀድመው ይጨርሳሉ፡፡ ውሃ እንደ ልብ ለመጠጣት እንኳ የሚሳቀቁ እንዳሉ ያውቃሉ?

ትዕግስትና መሰሎቿ አብዛኛዎቹ ሴቶች በወር አበባ ቀኖቻቸው ከትምህርት መቅረትን የተሻለ አማራጭ አድርገው ይወስዳሉ፡፡

በነዚህ ቀናት ሙሉ ቀን እየተማሩ…ሙሉ ቀን መፀዳጃ ቤት ሳይሄዱ መዋል የማይታሠብ ነው፡፡ አስፈላጊውን የመፀዳጃ ማቴሪያል የመሸመት አቅሙ እምን ያህል ነው? የሚለውን ደግሞ ማሰብ ነው…ዘንድሮ ያላሻቀበው የአንድ አትዮጲያዊ አማካይ የእድሜ ጣሪያ ብቻ ነው፡፡ለነገሩ በየት በኩል… "እንትን ሰፈር በቀን ሦስቴ የሚበላ ሰው አለ አይተሀል?" መባባል…በመጽሔቶቻችን የፊት ገጽ ላይ "ቁርሴ ቀለል ያለ ቅቤ ያልበዛበት ክትፎ…ምሳዬ ጭቅና ጥብስ…እራት ደግሞ…" እያለ የጃፓን ሱሞ ስፖርት ተወዳዳሪ የሚያክል የሀበሻ ሰው ምስል ስር "የእንትን ክፍለ ከተማ በቀን ሶስት ግዜ በዪ" የሚሉ ዜናዎችን ማንበባችን አይቀርም… ስንት ጉድ አለ ... ወደ ተነሳንበት ት/ት ቤት በአንድ ታክሲ እንመለስ…

ከትምህርት መቅረቱ 1 ቀን ብቻም ሳይሆን በወር ከ5 እስከ 7 ቀን ሊዘልቅ የሚችል ነው፡፡

እንዲህ ደግሞ አስቡ…ሴቷ አካል ጉዳተኛ የሆነች እንደውስ?

ይህኔማ በጥንቃቄ ግድግዳዋ ሳትነካኝ ጫፏን ብቻ ረግጨ የምትባለው አማራጭም ከናካቴው ድራሿ ይጠፋል፡፡
Photo courtesy of Water Aid Ethiopia

ከስር ቁጭ ብለው ከላይ የሚያንጠባጥቡ የዩንቨርሲቲዎቻችንን የዶርም መፀዳጃ ቤቶች ያየ ብዙ ሊል ይችላል፡፡

ሞት ይርሳኝ! የወንዶቹ ጠፍቶኝ ይመስላችኋል? እነሱ ቢያንስ በየጥጋጥጉ መፀዳዳት እንዲችሉ ተፈጥሮም ማህበረሰቡም አድልቶላቸዋል ብዬ ነው፡፡ እሱም የራሱ ጣጣ የራሱ መዘዝ እንዳለው ግን አንረሳም፡፡

እንቋጨዋ!

እንደኔ እንደኔ (አንቀፅ ባልጠቅስም ያለመቀበል መብታችሁ ይከበራል)…እና እንደኔ እንደኔ
ትምህርት ቤት ቢበዛ፣ እድሜው ለትምህርት የደረሠ ሁሉ ጆሮህን በእጅህ እየተባለ ትምህርት ቤት ቢገባ (እቺ ዘዴ አሁን ላይ በልደት ካርድ የተተካች ይመስላል)… አንድ መፅሐፉ አይደለም አንድ መምህር ለአንድ ተማሪ ቢዳረስ የሚፈለገው ውጤት ይመዘገባል፤ የሴቶችና የወንዶች እኩል የትምህርት ተሳትፎ ይመጣል ብሎ መጠበቅ የዋህነት እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
ይህ የኔ መጥፎ ምልኪ አይደለም…በአንድ ወቅት የሠማሁት ጥናት የመፀዳጃ ቤት ችግር በጠናባቸው ትምህርት ቤቶች ከሚማሩ ሴቶች አብዛኛዎቹ በወር ከ5 እስከ 7 ቀን፣ በ10 ወር የትምህርት ጊዜ ደግሞ ለሁለት ወራት እንዲቀሩ ያስገድዳቸዋል ይላል፡፡

ይህቺ ናት እኩል ተወዳዳሪነት!
ሴቶች  "ብርቅየው ሰላማዊ ሰልፍ ተፈቅዶ ሃሳባችንን ያለ አሳላፊ መንገር አስክንችል ይህችን ጦማር ለመንግስታችን አድረሽልን" ብለውኛል፡፡

እንዲህ ይነበባል….

"መንግስት ሆይ እኛ ሴቶች የመወዳደሪያ ሜዳው ከወንዶች እኩል እንዲሆንልን  እንሻለን፡፡ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍል ብቻም ሳይሆን ተጨማሪ መፀዳጃ ቤት መገንባት እንዳለበት እንዳትዘነጋ አደራ እንላለን!"

"ያለውን በአግባቡ እንድንጠቀምም ልቦናውን ይስጠን"……. አሜን!






ጋዜጠኛ ሃኒ ሰለሞን ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቀዋል፡፡ አሁን በሸገር ኤፍ.ኤም ሬዲዮ በጋዜጠኝነት በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሃሳብና አስተያየት ካለዎት በኢሜላቸው honeysolomon123@yahoo.com በፌስቡክ ገጻቸው https://www.facebook.com/honey.solomon.3 ሊያገኟቸው ይችላሉ፡፡

Saturday, April 13, 2013

እንከን አይወጣለትም!


የማወራችሁ ስለ 11 አመት ታዳጊ ነው፡፡ የኔ ግምት 8 ወይም 9 ነው፡፡ እሱ 11 ነኝ ስላለኝ ተጠቀምኩት እንጂ፡፡

    ከፒያሳ ወደ አዲሱ ገበያ መስመር ላይ በተለያዩ ታክሲዎች ላይ ወያላ ሆኖ ይሠራል፡፡
የመጀመሪያ ቀን ፒያሳ "አዲሱ ገበያ ሰሜን ሆቴል የሞላ የሞላ 2 ሠው" እያለ ደጋግሞ ሲጠራ ይህ ልጅ ወያላ ነው ለማለት ተቸግሬ ነበር፡፡ ታክሲ ውስጥ ያለው ሁሉ በአግራሞት እያየው ከንፈር ይመጣል፡፡

     ታዳጊው ከእድሜው በታች በጣም ቀጫጫ ነው፡፡ ጉዞ ጀምረን ገንዘብ ሲሰብሰብ እጁ ዝርዝር ሳንቲሞች ለመያዝ ተቸግሮ አሁንም አሁንም ኪስ ወደ ተሞላች ሱሪው እጁን ይሠዳል፡፡ ድንገት ስራውን ዘንግቶ በታክሲ ካሉት ህፃናት ጋር ይጫወታል፡፡ ደግሞ መለስ ይላል፡፡ ታክሲ ውስጥ ካሉት አብዛኛዎቹ ያላቸውን መልስ ሳይቀበሉ ትተው ወረዱ፡፡ከዛ በኋላ ከአማኑኤል ጋር ደጋግመን ተገናኝተናል፡፡

እንዲህ ያለውን አቅምና እድሜን ያላገናዘበ የጉልበት ስራ ለኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ5 እስከ 14 የሆኑ 60 በመቶ ህፃናት ይጋሩታል፡፡ያውም በከፋ መንገድ፡፡  

     ይህ በአለም የህፃናት ጉልበት ከሚበዘበዝባቸው 10 ፊት አውራሪ የአለም አገሮች ኢትዮጵያን አንዷ  አድርጓታል፡፡
በሒልተን ሆቴል በተዘጋጀ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን የተመለከተ ስብሠባ ላይ እንድሳተፍ ተጠራሁ፡፡ እንደ ጋዜጠኛ ብዙ ልሠማ ሄድኩ…ግን ብዙ እንድናወራ የሚጠበቅበት ሆኖ አገኘሁት፡፡ ‹‹ቶክሾው›› መሆኑ ነው፡፡
ፕሮግራሙን የሚመራው ጋዜጠኛ ... (አሁን ስም ምን ያደርጋል?) ይህ የሚያክል ትልቅ ሀሳብ በ3 ደቂቃ እንዲገባደድ የሚናገሩትን ጋዜጠኞችና ‹ባለድርሻ አካላት
(የሚመለከታቸው እንደማለት ነው)፤ አፍ አፋቸውን ይላል፡፡ የሚጀመር እንጂ የሚያልቅ ሀሳብ ጠፍቷል፡፡  ባለሙያዎቹ እንዲህ አይነት ጥፋተኞችን ለመቅጣት በቂ ኧረ እንደውም ከዛ በላይ ህግ ወጥቷል ግን ተፈፃሚ አይደለም ይላሉ፡፡ አብዛኛው ሰው ግን የግንዛቤ እጥረት›› የምትለው ሃሳብ ላይ የሙጠኝ ብሎ ይዘምራታል፡፡

 ወይ ጣጣ
     ‹‹የግንዛቤ እጥረት የግንዛቤ እጥረት "የግንዛቤ እጥረት"  ይላል፡፡ እንዴት እጅ እጅ ይላል ይህ ቃል? በግንዛቤ እጥረት የተናገሩት ይሆናል ብልን እንለፈው፡፡ እኛ ሀገር ሁሉም ነገር በግንዛቤ እጥረት የመጣ ነው፡፡

እድሜያቸው ከ15 አመት በታች የሆኑ ልጆችን ከባባድ ስራ ማሰማራት ያስቀጣል፡፡ በህግ ተደንጓል! አንቀጽ ወጥቶለታል! ወንጀል ነው!
በየቤታችን አንድ ለልጅ አቃፊ፣ አንድ እግር አጣቢ፣ እያልን ህፃናትን ከገጠር ስንመለምል ወይም ሽሮሜዳን ያጥለቀለቁትን የሚታዩና የማይታዮ ህፃናትን ጉልበት ስንበዘብዝ እንታያለን፡፡ ድርጊቱን የሚፈፅሙት እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ወጪ ለመቆጠብ፤ የፍላጐት ያህል ጉልበት ለመበዝበዝ፤ ትርፍ ለማጋበስ ይህ ሁሉ ጥቅም ነው፡፡
ሲጋራ ማጨስ እንደሚጐዳ አጫሹ ያወቀዋል ግን ያደርገዋል፡፡ ተያያዥ የሆነ  አካባቢያዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊኖርውም፣ ይህ ሰው የሚጐዳው ራሱን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህን አጫሽ የግንዛቤ እጥረት አለበት ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ በሌሎች ህይወትና ሬሳ ላይ ቤቱን የሚያቆምና ህንፃ የሚሠራን እንዴት ግንዛቤ  አጥሮት ነው ተብሎ "እንከን አይወጣለትም" የተባለ ህግ ሳይፈፀም ይቀራል?
አታምርሪ እንደምትሉኝ አውቃለሁ፡፡ ግን ልቀጥል ትንሽ እድል ስጡኝ፡፡
ሌላው ተደጋግሞ ሲነሳ የነበረው ምን መሰላችሁ? "ህብረተሰቡን ለወንጀል ተባባሪ ሆነ ጥፋተኛን አያጋልጥም" የሚል ወቀሳ ነው››
ሀገር ያወቀው ፀሃይ የሞቀው የአደባባይ ጉዳይ ከህዝቤ ካልሠማሁ አላምንም የሚል ከአይኑ ይልቅ ህዝቡን የሚያምን ብቸኛ መንግስት የኛ ሃገሩ ይመስለኛል፡፡

ስለ ኢትዮጵያ ማውራት ይቅር .... አዲስ አበባ ላይ ሰብሰብ እንበል፡፡ ስለሽሮ ሜዳዎቹ ህፃናትም አናንሳ .... በየቤቱ ተጫውተው ሳይጠግቡ አጫዋች የሆኑ፣ ቤታችንን ቀጥ አድርገው የሚያስተዳድሩ፣ የንዴትና ብስጭታችን ማራገፊያ የሆኑ ህፃናት ጉዳይንም ተዉት፡፡  
..... የወያላዎቹንም ህፃናት ጉዳይ አታንሱት፡፡ ሁሉንም እርሱት፡፡

ጋዜጠኝነት እግር ጥሎ የሚያደርሠን ቦታ ብዙ ነው፡፡
ይህ የመስሪያ ቤቶች የሻይ ክበብን ይጨምራል፡፡ በብዙዎቹ ደርሻለሁ፡፡ የሚያስተናግዷችሁ፣ ከለሊት ጀምሮ የምግብ እቃ፣ ወለልና ጠረጴዛ ሲያፀዱ የሚውሉ እነዚሁ እምቦቃቅላ ህፃናት መሆናችሁን ልብ ብላችኋል? ... እውነት እስኪ ስራዬ ብላችሁ ተመልከቱት፡፡
ስለነዚህ ህፃናት አዝነው ሳያበቁ፣ ያሉበት ክበብ መዝናኛ ቤቶች የህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚንስቴር ወይም ቢሮ መሆኑን ቢያውቁ ምን ይሠማዎታል፡፡
ማታ በቴሌቭዥንዎ የዜና ሰዓት ‹‹የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ይበቃ›› የሚል ቲሸርትና ኮፊያ አድርጐ ንግግር ሲያደርግ ያያችሁት ሰው ‹‹አንተ ማነህ..... እያለ ትዕዛዙን ሲያዥጐድጐድ ይደመጣል፡፡

     በርግጥ እነዚህን ህፃናት አትወይሉ፣ አታስተናግዱ፣ አትጠቡ፣ አታፅዱ ማለት አትበሉም ማለት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ይህ ህይወት ወደው ሳይሆን ኑሮን ለማሸነፍ ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ ጥርሱን ያገጠጠውን ድህነት ለማምለጥ የገቡበት ነው፡፡

     አማኑኤል በቋሚነት የሚኖርበት ታክሲ ሳይኖረው በአጋጣሚ ከወያላቸው ተጋጭተው ወይም በሌላም ምክንያት ያለ ገንዘብ ያዥ የሚወጡ ተሸከርካሪዎች ላይ እየተገለባበጠ እንደሚሠራ ያወኩት  በቅርብ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ከብዙ መሰሎቹ ተጋፍቶ የሚያገኘው ሎተሪ ነው፡፡ አብዛኛው ባለስልጣን ለስርዓቱ ስም ሲል ችግሩን አጐልቶ ማውራት ይፈራል፡፡ ለውጡ ላይ ከስር ከስር እየሠራ ነው እንዳይባል የሚመለከተው በማይመለከተው ጉዳይ ተጠምዷል፡፡

     የስርዓቱ እድሜን የሚያረዝም የሚመስል አንድ ጉዳይ ይዞ ችክ ምንችክ ከማለት ለህዝቡ ለውጥ የሚመጣው ላይ መረባረቡ ይሻላል፡፡ እንደኔ ለውጡ እድሜ ማምጣቱ አይቀርምና፡፡
እናንተ ምን ታስባላችሁ?  




ጋዜጠኛ ሃኒ ሰለሞን ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቀዋል፡፡ አሁን በሸገር ኤፍ.ኤም ሬዲዮ በጋዜጠኝነት በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሃሳብና አስተያየት ካለዎት በኢሜላቸው honeysolomon123@yahoo.com በፌስቡክ ገጻቸው https://www.facebook.com/honey.solomon.3 ሊያገኟቸው ይችላሉ፡፡

Saturday, April 6, 2013

“ብር ይዞ ይመጣል”





   ከአመታት በፊት በአንድ አጋጣሚ በአውሮጳ በአንዱ ከተማ ለጥቂት ቀናት ያገኘነው ወጣት እጅግ ለጋስ በሆነው በአገራችን ልጆች መስተንግዶ ካስተናገደን በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮች አውጥቶ ለአባቴ ስጡልኝ አለን፡፡ የወጣቱን ልጅ ኑሮና እጅግ የበረታ የሥራ ድካም በሁለት ቀን ዕድሜ ጥሩ አድርገን አይተነው ነበርና ምነው አይበዛም? አንተ እዚህ አልተመቸህ? አልነው በማያገባን ገብተን፡፡ አባቴ የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ውጤት ጥሩ ስላልመጣልኝ ለዓመታት እቤት ውስጥ እውል ነበርና፤ እግቢያችን ውስጥ ያለውን የኰክ ዛፍ እያሳየ “አንተና ይሄ የኮክ ዛፍ አንድ ናችሁ አታፈሩም”! ይለኝ ስለነበር እዚህ መጥቼ ያጠራቀምኩትን የመጀመሪያ ገንዘብ ማፍራቴን እንዲያይ መላኬ ነው፡፡ ማለቱን መቼም አልረሣውም ፡፡

   በየአገሩ የተበተኑት ኢትዮጵያውያን ከያሉበት አገር ወደ አገር ቤት ገንዘብ ሲልኩ ስሰማም ሆነ ሳይ የዚያ የወጣት አነጋገር በሃሳቤ ይመጣል፡፡ በየጊዜው የሞራል ስብራት ያደረስንባቸው ልጆቻችን የልጅነት ወዛቸውንና ጉልበታቸውን እያፈሰሱ ያላቸውን ጥሪት እየላኩ የሞራል ስብራታቸውን እየጠገኑ፣ ቁጭታቸውን እየተወጡ ይሆን?

   የአለም ባንክ የቅርብ  ጊዜ መረጃ 215 ሚሊዮን ሰዎች ከትውልድ አገራቸው ውጪ ይኖራሉ ይላል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ወደየትውልድ አገራቸው የሚላከው ገንዘብ ከተለያዩ አገሮች በልማት ስም ከሚሰጠው ዕርዳታ በሦስት እጅ ይበልጣልም ይላል፡፡ ይሄም በገንዘብ ሲሰላ በ2011 ብቻ 372 ቢሊዮን ዶላር በ2012 530 ቢሊዮን እንደደረሰ የአለም ባንክ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ቁጥሩም በየዓመቱ እየጨመረ እንደሚሄድ ያሳያል፡፡ ይሄ እንግዲህ እንደ አለም ባንክ መረጃ፤ ፀሐይ ሞቆት አገር አውቆት በባንክ በኩል የሚካሄደውን የገንዘብ ዝውውር እንጂ የአድርሱልኙንና ሌላ ሌላውን አይጨምርም፡፡


  ይሄን መረጃ መነሻ አድርገው የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ከበለፀጉ አገሮች ከሚላከው የገንዘብ እርዳታ ይልቅ በየአገሩ ኗሪ ከሆኑ ስደተኞች የሚላከው ገንዘብ ከዕርዳታው ድጐማ በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ከሆነ የትኛው አማራጭ ይበጃል? እያሉ ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የሚበጀው በብዙ የእርዳታ ውለታ የማይታሠረው የአገር ልጆች በፈቃዳቸው የሚልኩት ገንዘብ ይመስለኛል፡፡

እነዚህ ኤኮኖሚስቶች በግልጽ የማይናገሩት፣ ግን “ስደተኞች ወደ አገራቸው የሚልኩት ቢሊዮኖች ዶላሮች ሳቢያ የለጋሽ አገሮች እርዳታ ጥላ ጥሎበታል” በሚለው ዜና ሥር ሥር የሚሄድ አንድ ስጋት ያለ ይመስላል፡፡ ምናልባት ስጋቱ እነዚህ እርዳታ ጠባቂ አገሮች ሁለት ጥቅም ይዞ የሚላክላቸውን እርዳታችንን ከቁብ መቁጠር ያቆማሉ የሚል ነው እንበል? ማን አላችሁ? ተብሎ ቢጠየቅ እገሌ በማይባልበት የድፍረት አነጋገርም “የኛም በፖለቲካ ወዘተ ወዘተ ተጽእኖ የማሳደር አቅማችን እየቀነሰ ይመጣል” የሚል ይመስላል እንበል፡፡ እንግዲህ ከተወላጆች ወደ አገር ቤት የሚላከው ገንዘብ እያደገ ከሄደ ብዙ የለጋሾችን እጅ ጠባቂ አገሮች ጠባያቸው መቀየሩ አይቀሬ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ አገሮች ርዳታውን ከአገሬ ልጆች አገኘዋለሁ እያሉ እያስፈራሩ መሆኑ ይነገራል፡፡

   በእርዳታም ይሁን በውጭ ኢንቨስትመንት ተደምሮ ከሚመጣው ገንዘብ ይልቅ በአገር ልጆች ወደ አገር ቤት የሚላከው ገንዘብ ከሚበልጥባቸው አገሮች መካከል ባንግላዴሽ፣ ሜክሲኮንና ሴኔጋልን መጥቀስ ይቻላል፡፡  በተለይ ጠዋት ለቤተሰብ የተላከው ገንዘብ ምሽት ላይ በኢንተርኔትና በስካይፕ ቤተሰብ ምን እንዳደረገበት በአይን ሲታይ ላኪውን ይበልጥ ማስደሰቱና ማርካቱ ላኪዎችን ማትጋቱ በየዓመቱ የገንዘቡን መጠን አሳድጐታል ይላሉ በዋሽንግተን የ Center for Global Development አጥኚ ማይክል ክሌመንስ፡፡

የማህበረሰብ ተሟጋች ተቋማት ደግሞ ይሄ ገንዘብ በሥራ ሰበብ ብዙ እንግልትና ጉዳት የሚደርስባቸውን በየአገሩ የሚሰደዱ ዜጐችን መከራ ሊያስረሣ አይገባም፡፡ የኤኮኖሚ ስደተኞች መብት መከበር ይኖርበታል ይላሉ፡፡  ለመቆጣጠር አለም አቀፍ ሕግ ወጥቷል፡፡ ብዙ መንግሥታት ግን አልፈረሙትም ከእነዚህ መካከልም አሜሪካና የአውሮፓ አገሮች እንዲሁም የገልፍ አገሮች ይገኙበታል፡፡

በእኛም “አገር ሣሩን አየህና” እየሆነ ብዙ ወጣቶች በየድንበር ኬላውና በየአገሩ የሚደርስባቸውን እንግልት በየቀኑ እንሠማዋለን፡፡ ይሄን የስደተኛ ሠራተኞችን ችግር  በየአገሩ የተሠራጩትን የአገር ልጆች ገንዘባቸውን መውደድ ብቻ ሳይሆን ለደህንነታቸውም መከራከር ይገባል፡፡ ያገራችን ተረት ምን ነበር?
      የአገር ልጅ
      የማር እጅ?
እናንተስ ምን ትላላችሁ?






ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የቆዩ የሬዲዮ ጋዜጠኛ ናቸው፡፡ ላለፉት አስራ ምናምን አመታት በየጨዋታ እንግዳ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ለጋዜጠኛ መዓዛ የምንለው አለን የምትሉ meaza.birru@shegerfm.com ይጻፉ፡፡ ወይንም በዚሁ ብሎግ ላይ አስተያየታችሁን ማስፈር ትችላላችሁ!