Total Pageviews

Saturday, March 30, 2013

ቁጭ በል-ካ በመሬት

    ጊዜው ትንሽ ረዘም ብሏል የደርግ ጊዜ በመባል የሚታወቀው ወቅት ነው፡፡ ሁኔታው የተፈጠረው ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ድሬዳዋ በሚሄድ ባቡር ላይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ ጅቡቲ መንገደኛ ይዞ የሚጓዝ ባቡር ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ሲልም የማታው ባቡር መኘታም ነበረው፡፡ ለማንኛውም መነሻቸውን ከአዲስ አበባ ያደረጉ ተሳፋሪዎች በዋዜማው በአዲስ አበባው ላጋር ባቡር ጣቢያ ቲኬታቸውን ረጅም ሠልፍ ተሰልፈው ቆርጠው በመሄጃቸው ቀን ሌሊት በ11 ሰዓት ሄደው ተሣፍረው ናዝሬት ደረሱ፡፡  የትዕዩንቱ ባለታሪኮች አንዲት ሴትና ሕፃን ልጇ፣ አንድ ወጣት፣ ሌሎች ተሣፋሪዎች፣ እንዲሁም ፈንጠር ብለው የተቀመጡ የአደሬ አዛውንት ናቸው፡፡ ወጣቱና እመጫቷ አንድ ወንበር የተጋሩ ቢሆንም ወጣቱ ለእመጫቷ ከነልጇ እንዲመቻት ወንበሩን ለቆ በፉርጐው በራፍ ላይ ቆሟል፡፡ ባቡሩ ናዝሬት ላይ ሲቆም አንድ ተሣፋሪ በዚህኛው ፉርጐ ይገባል፡፡ ዙሪያ ገባውን ይመለከታል፡፡ ትርፍ ወንበር ያጣል፡፡ ትርፍ ነው ብሎ የገመተውን ቦታ እናቲቱና ልጅ የያዙትን

                  “ልጅሽን እቀፊና እኔ ወንበሩ ላይ ልቀመጥ” ይላል፡፡
    በዚህ ጊዜ ቦታውን የለቀቀው ወጣት ፈጠን ብሎ ጠጋ ይልና “እኔ እንዲመቻት ብዬ ነው የለቀቀሁላት እንጂ ለመቀመጥማ ቦታው የኔ ነው ይላል፡፡ አንድ ሁለት ሲባባሉ ጠቡ የሁሉም የባቡር ተሣፋሪ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ተሣፋሪው ግለሰብ በየዘመኑ በአገራችን ብቅ የሚሉና “የዘመኑ ሰው” በመባል የሚታወቁ ልበ ሙሉዎች አንዱ መሆኑን በጐኑ የታጠቀው መሣሪያ ኮቱን ገለጥ አድርጐ በማሳየት በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ቦታ በቃል ብቻ ሳይሆን በድርጊት ያሳያል፡፡ አብዛኛው ገላጋይ ድምፁን እየቀነሠ ይሄዳል፡፡ ፍጥጫው ባለወንበሩ ወጣት፣ የሕፃኑ እናትና በባለ ሽጉጡ ልበ ሙሉ መካከል ይጦፋል፡፡ እስካሁን ቃላቻውን ያልሰጡት በመስኮት ወሬ እያዩ ጥርሳቸውን የሚፍቁት አዛውንት “የኔ ወንድም” ብለው ጉሮሮአቸውን አጥርተው በጉዳዩ ለመጀመሪያ ጊዜ ጣልቃ ይገባሉ፡፡

                        “እስቲ ና ወዲህም” ይላሉ፡፡

    ጐበዙ የባቡር ላይ ጀግናም ምናልባት ፍትህ ከእሳቸው አገኝ ብሎ ፊቱን ወደ አዛውንቱ ያዞራል፡፡ እሳቸውም የአደርኛ ለዛ በብርቱ በተጫነው አማርኛ (ተሰልፈው ቲኬቱን ሲገዙ ጀምሮ ጠዋት ሲሳፈሩ የነበረውን ድካምና እንግልት በዝርዝር ያስረዱታል፡፡ አንተ አሉት “እኛ ሌሊት 10 ሠዓት ላይ ተነስተን ወረፋ ይዘን ስንሳፈር ተኝተሃል፡፡” “አሥራ አንድ ሰዓት ላይ ባቡር ላይ ስንወጣም ተኝተሃል፡፡ እንቅልፍህን ጠግበሃል፡፡ ቁርስ በልተሃል፡፡ ሻሂ ጠጥተሃል፡፡ ሲጋራህን አፍህ ላይ አድርገሃል፡፡ እና፡፡ ይላሉ የአደሬው አዛውንት (ወደ ፍርድ ውሳኔያቸው አንደርድሬ ልውሰዳችሁና)  “የኔ ወንድም! ቁጭ በልካ በመሬት!” አሉና ፊታቸውን ወደ ባቡሩ መስኮት አቃንተው እየተመለከቱ ጥርሣቸውን መፋቅ ቀጠሉ እኛ የተጓደለብን ምቾት ስላገኘህና ትርፍ ወንበርም ባለመኖሩ ወንበር ከሌለ የሚገባህ፣ መሬቱ ነውና መሬት ላይ ቁጭ በል ማለታቸው ነው፡፡ የፍርጐው ሰው ሁሉ ይስቃል፡፡ መንግሥቱ ለማ “ብራቮ” ተባለ ነው ያሉት? በባሻ አሸብር ላይ? እንደዛ ተባለ፡፡ ሰውየው ኩምሽሽ ይላል፡፡ እመጫት ከነልጇ ተስፋፍታ ትቀመጣለች ፍርጐው ውስጥ ሠላም ይሠፍናል፡፡ የዚህ ዳኝነት ባለቤት እኒያ “ቁጭ በል ካ በመሬት” ያሉ አዛውንት ናቸው፡፡

ተንደርድረን ወደዚህ ዘመን እንምጣ፡፡ የተፈጥሮ ሕግ ነውና በየቀኑ በተለያዩ የኑሮአችን ግንኙነቶች እንዲህ ያሉ ዘመናይ የሰው መብት ተጋፊ ጉልቤ ማን አለብኝ ባዮች ያጋጥሙናል፡፡ በቅርቡ በአንድ ጋዜጣ ታክሲ ላይ ሽጉጣቸውን በገንዘብ አስከፋዩ ላይ ያወጡ ሰው ተከሰሱ የሚል ዜና ተመልክቻለሁ፣ በየቡና ቤቱ ይሄኛው  ዘፈን ለምን ተዘፈነ ብለው ቡራከረዩ የሚሉ፣ በጐናቸው የታጠቁትን ሽጉጥ እያሳዩ የሚገሠሉ፣ በየመንገዱ የወጣት ሴቶችን ስለማዊ ጉዞ የሚያውኩ፣ ጊዜ በሠጣቸው ሥልጣን የሰው አጥር የሚገፉ ማን ይናገረኛል ባይ ጡንቸኞች፣ ያጋጥሙናል፡፡ እናስ እንደ እኒያ አዛውንት “ቁጭ በል ካ በመሬት” የሚል ብዙ ሰው አለ?

አለፍ ከፍ እንበል ባለሥልጣን ሲሳሳት፣ የሥልጣን ብልግና ሲፈፀም፣ ባለ ገንዘብ ከሕግ ውጪ ሲሆን፣ ጐረምሶች መሬቱ ጠበበን ሲሉ እስቲ ቆይ እዚች ላይ አቁሙ የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ?
አለም የለምም የምትሉኝ ጻፉልኝ!




   ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የቆዩ የሬዲዮ ጋዜጠኛ ናቸው፡፡ ላለፉት አስራ ምናምን አመታት በየጨዋታ እንግዳ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ለጋዜጠኛ መዓዛ የምንለው አለን የምትሉ meaza.birru@shegerfm.com ይጻፉ፡፡ ወይንም በዚሁ ብሎግ ላይ አስተያየታችሁን ማስፈር ትችላላችሁ!