ዛሬ ወደ ትምህርት ቤታችሁ በምናብ
ልመልሳችሁ፡፡ ስንቱን ማስታወስ ይቻላል? ከበር ላይ ያሉት ጥበቃዎች፤ የመማሪያ ክፍሎቻችሁ፤ መምህራን (የምትወዷቸው የምትጠሏቸውንም
ሊሆን ይችላል)፤ ቤተ-መፅሐፍት፤ ካፊቴሪያው፤ ሽንት ቤቱ...
"ቁም!" አሉ
ፕሮፌሰር…እደግመዋለሁ! አላዝቤም አልጠቀምም፡፡ ሽንት ቤቱ...እዛው እንቆያለን… ሽንት ቤት እንቆያለን ... እንቆያለን ... እንቆያለን…አፍንጫ መያዝ የተከለከለ ነው!
... እንቆያለን…እንቆያለን…በቃ አሁን ይበቃናል...ኡፍፍፍፍፍፍፍፍፍ…ምነው በረጅም ተነፈሳችሁ?
ትዝታው እራሱ ይጨንቃል አይደል?
የመንግስት ትምህርት ቤቶችን የመፀዳጃ ቤት ችግር ያየ የደረሰበት ያውቃል፡፡ በኛ ሃገር ያውም በመንግስት ትምህርት ቤቶች
ፊደል ቆጥሮ ስለመፀዳጃ ቤቶች ጥሩ ትዝታ ያለው ካለ በጆሮዬ ሹክ ይበለኝ… በአደባባይ የምነግራችሁ ይህ ሰው ወይ ሀገር ቤት አልነበረም
ወይም ቤተሠቦቹ ከላይኛው መደብ ስለነበሩ እንትን ትምህርት ቤት ይሆናል የተማረው፡፡ ምክንያቱም ይህ ችግር የአብዛኛው አትዮጵያዊ
ታሪክ ነው ለማለት እደፍራለሁ፡፡
ስለ ትምህርት ቤቶች እናውራ
ብለን የለ?....ስለመፀዳጃ ቤቶቻቸው ነው፡፡ መቼም ስንቶቻችሁ ፊታችሁ ጭፈግግ እንዳለ የምታነቡት ፅሑፍ ይቁጠረው….እኔማ የት
አያችኋለሁ?
ዛሬ ላይ ትምህርት ቤቶች በአዲስ አበባ እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ 903 አፀደ ህፃናት 730 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እና 169 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከፍቷል፡፡
የመንግስትም የግልም ማለቴ ነው፡፡
ትኩረቴ 65 በሚሆኑት 2ኛ ደረጃ
የመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ ነው፡፡ እዛ ጉዳይ አለኝ!
ከትምህርት ቤት ቁጥር መብዛት
ጋር ቅሬታ ያለን አይመስለኝም ....እኔ በግሌ የለኝም፡፡ ለስንቱ መንገድ አሳጥሯል፡፡
"እያደር
ትመጣለች" የተባለችውን ጥራት ግን እየጠበቅንሽ ነው በሏት፡፡
ቀርታም እንደሆን፤የደረሠችበትን
የሚያውቅ ካለም ይንገረን፡፡
ትዕግስታችን ተሟጠጠ እኮ...
ለዛሬ ወጋችን መነሻ የሆነች አንድ ልጅ ላስተዋውቃችሁ፡፡ ትዕግስት ትባላለች፡፡..... ሰሞኑን ወደ አንዱ ክልል ከተማ
ለስራ ሄጄ ነበር… እግር በጉዞ ብዛት ቢያጥር ኖሮ አንገቴ ጋ ሊደርስ ሲል የሆነ ቦታ አረፍ አልኩ፡፡ ትዕግስትን ተዋወቅኩ፡፡
የድንጋይ ንጣፍ ለሚሠሩ ወጣቶች
ሻይና የተጠበሰ ብስኩት ትሸጣለች፡፡ ቀኑ ሰኞ ነው፡፡ ከብዙ
ጨዋታ በኋላ ምነው ከትምህርት ቀረሽ አልኳት፡፡ ጊዜ አልፈጀባትም
"የወር አበባ ላይ ስለሆንኩ ነው" አለች፡፡
አንድ ወዳጄ ‹‹ ቀይ ሽብር ሲፋፋም›› ትለዋለች ይህንን
ሰሞን… ልዋሰው ለአሁን ብቻ!
እንደ አብዛኞዎቹ የአዲስ አበባ የመንግስት ትምህርት ቤቶች
የትዕግስት ትምህርት ቤት መፀዳጃም እንኳን እንደዚህ ባለው ‹‹የቀይ ሽብር›› ቀን ይቅርና እንዲሁ በአዘቦቱም ከደጁ አትጣለኝ የሚባልበት
ነው፡፡
የትምህርት ቤቶቹ መፀዳጃ ቤቶች የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን
ፍሳሽ መጣጭ ቦቴዎች ናፍቋቸዋል፡፡
ወለሉ መረገጫ የሚባል ክፍት ቦታ የሌለው….. ግድግዳው
በእድፍ የተሞላ ነው፡፡
ቅፍፍ ይላል አይደል? ይደብራል!
ግን እውነት ነው፡፡
ይህ የትዕግስት ብቻ ታሪክ አይደለም፡፡ ብዙ ሴቶች በደህና
ቀናችሁ ለውሃ ሽንት እንኳ ወደ መፀዳጃ ቤት ላለመሄድ ጉዳያችው ከበር ውጪ ቀድመው ይጨርሳሉ፡፡ ውሃ እንደ ልብ ለመጠጣት እንኳ
የሚሳቀቁ እንዳሉ ያውቃሉ?
ትዕግስትና መሰሎቿ አብዛኛዎቹ ሴቶች በወር አበባ ቀኖቻቸው
ከትምህርት መቅረትን የተሻለ አማራጭ አድርገው ይወስዳሉ፡፡
በነዚህ
ቀናት ሙሉ ቀን እየተማሩ…ሙሉ ቀን መፀዳጃ ቤት ሳይሄዱ መዋል የማይታሠብ ነው፡፡ አስፈላጊውን የመፀዳጃ ማቴሪያል የመሸመት አቅሙ
እምን ያህል ነው? የሚለውን ደግሞ ማሰብ ነው…ዘንድሮ ያላሻቀበው የአንድ አትዮጲያዊ አማካይ የእድሜ ጣሪያ ብቻ ነው፡፡ለነገሩ በየት
በኩል… "እንትን ሰፈር በቀን ሦስቴ የሚበላ ሰው አለ አይተሀል?" መባባል…በመጽሔቶቻችን የፊት ገጽ ላይ
"ቁርሴ ቀለል ያለ ቅቤ ያልበዛበት ክትፎ…ምሳዬ ጭቅና ጥብስ…እራት ደግሞ…" እያለ የጃፓን ሱሞ ስፖርት ተወዳዳሪ
የሚያክል የሀበሻ ሰው ምስል ስር "የእንትን ክፍለ ከተማ በቀን ሶስት ግዜ በዪ" የሚሉ ዜናዎችን ማንበባችን አይቀርም…
ስንት ጉድ አለ ... ወደ ተነሳንበት ት/ት ቤት በአንድ ታክሲ እንመለስ…
ከትምህርት መቅረቱ 1 ቀን ብቻም ሳይሆን በወር ከ5 እስከ
7 ቀን ሊዘልቅ የሚችል ነው፡፡
እንዲህ ደግሞ አስቡ…ሴቷ አካል ጉዳተኛ የሆነች እንደውስ?
ይህኔማ በጥንቃቄ ግድግዳዋ ሳትነካኝ ጫፏን ብቻ ረግጨ
የምትባለው አማራጭም ከናካቴው ድራሿ ይጠፋል፡፡
Photo courtesy of Water Aid
Ethiopia
ከስር ቁጭ ብለው ከላይ የሚያንጠባጥቡ የዩንቨርሲቲዎቻችንን
የዶርም መፀዳጃ ቤቶች ያየ ብዙ ሊል ይችላል፡፡
ሞት ይርሳኝ! የወንዶቹ ጠፍቶኝ ይመስላችኋል? እነሱ
ቢያንስ በየጥጋጥጉ መፀዳዳት እንዲችሉ ተፈጥሮም ማህበረሰቡም አድልቶላቸዋል ብዬ ነው፡፡ እሱም የራሱ ጣጣ የራሱ መዘዝ እንዳለው
ግን አንረሳም፡፡
እንቋጨዋ!
እንደኔ
እንደኔ (አንቀፅ ባልጠቅስም ያለመቀበል መብታችሁ ይከበራል)…እና እንደኔ እንደኔ
ትምህርት ቤት ቢበዛ፣ እድሜው ለትምህርት የደረሠ ሁሉ
ጆሮህን በእጅህ እየተባለ ትምህርት ቤት ቢገባ (እቺ ዘዴ አሁን ላይ በልደት ካርድ የተተካች ይመስላል)… አንድ መፅሐፉ አይደለም
አንድ መምህር ለአንድ ተማሪ ቢዳረስ የሚፈለገው ውጤት ይመዘገባል፤ የሴቶችና የወንዶች እኩል የትምህርት ተሳትፎ ይመጣል ብሎ መጠበቅ
የዋህነት እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
ይህ የኔ መጥፎ ምልኪ አይደለም…በአንድ ወቅት የሠማሁት
ጥናት የመፀዳጃ ቤት ችግር በጠናባቸው ትምህርት ቤቶች ከሚማሩ ሴቶች አብዛኛዎቹ በወር ከ5 እስከ 7 ቀን፣ በ10 ወር የትምህርት
ጊዜ ደግሞ ለሁለት ወራት እንዲቀሩ ያስገድዳቸዋል ይላል፡፡
ይህቺ ናት እኩል ተወዳዳሪነት!
ሴቶች "ብርቅየው ሰላማዊ ሰልፍ ተፈቅዶ ሃሳባችንን ያለ አሳላፊ መንገር አስክንችል
ይህችን ጦማር ለመንግስታችን አድረሽልን" ብለውኛል፡፡
እንዲህ ይነበባል….
"መንግስት ሆይ እኛ ሴቶች የመወዳደሪያ ሜዳው
ከወንዶች እኩል እንዲሆንልን እንሻለን፡፡ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍል
ብቻም ሳይሆን ተጨማሪ መፀዳጃ ቤት መገንባት እንዳለበት እንዳትዘነጋ አደራ እንላለን!"
"ያለውን በአግባቡ እንድንጠቀምም ልቦናውን ይስጠን"…….
አሜን!
ጋዜጠኛ ሃኒ ሰለሞን ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቀዋል፡፡ አሁን በሸገር ኤፍ.ኤም ሬዲዮ በጋዜጠኝነት በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሃሳብና አስተያየት ካለዎት በኢሜላቸው honeysolomon123@yahoo.com በፌስቡክ ገጻቸው https://www.facebook.com/honey.solomon.3 ሊያገኟቸው ይችላሉ፡፡
honey, u remind us of our childhood,sply when i c z pic teardrop in my eye,u can feel something in her face.anyway honey it good job,keep it up,i think honey even u go zer(hawassa) 4 dat bad election news,but @ least u profit dis 4 us.Thanks
ReplyDeletesan diego,CA
ፊት ሚሰጨፈግግ ሚያዘናና ሃሪፍ ጹፍ በራቮ ሃኒ ! በርቺ ግን እንደዚህ አይጠር …
ReplyDeleteአነገብጋቢና መሰረት ያለው እይታ፡፡ በተደጋጋሚ ከት/ት ሚ/ር ጋር በአጠቃላይ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም ግምገማ ላይ ተሳትፈአለው፡፡ ችግሩንም በመረጃ በተደገፈ መልኩ አውቀዋለሁ ግን እንደአንቺ በዚህ መልኩ አልገለጽኩትም፡፡ በዚሁ ቀጥይ
ReplyDeleteምንም አዲስ ነገር
ReplyDelete