Total Pageviews

Wednesday, June 19, 2013

ትዝብት በእንዳለ : እናት ለምን ትሙት ትሂድ አጎንብሳ,,,


 አዲስ አበባ ግንቦት 28፣2005 ዓ ም  :: መንግስት ባወጣው የ 10/ በ90፣20/በ80፣40/በ60 አዲስ ቤት መስሪያ የቁጠባ ደብተር ለማውጣት ከክፍለ ሀገር በመጣው ቀን በበነጋው  ዕለተ ዕሮብ ግንቦት 28፣2005 ነበር:: ቃሊቲ ሚድ ሮክ አከባቢ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ  እኔም እንደዜጋና እንደ አንድ አዲስ አበባ ነዋሪ ቤት መስሪያ የሚሆነኝን ቁጠባ ደብተር ለማውጣት ታላቅ ወንድሜ ከለሊቱ 9:00 ሰዓት ከቤት ወጥቶና 45ኛ ሆኖ በተመዘገበልኝ ተራ ጠብቄ ለመመዝገብ ነበር እዚያ የሄድኩት::  
ታዲያ ባንኩ ከዋናው መንገድ ማለትም ከቃሊቲ ወደ ደብረ ዘይት ከሚወስደው አውራ ጎዳና በስተ ቀኝ ዳር ላይ የሚገኝ ሲሆን :: ከተመዝጋቢው ህዝብ ብዛት የተነሳ ሊመዘገብ ሰልፍ ከያዘ ሰው በተጨማሪ ሰልፍ ሳይዝ የቆመው ሰው አስፋልቱ ጠርዝ ድረስ በቡድን በቡድን እየሆኑ በቤቱ ምዝገባ ላይ የየራሱን ወግ ይዟል ::
አንዱ ቡድን ስለ ህገ ደንቡ እንዲያስረዳ አንዱ የቡድን አባል በጠየቀው ጥያቄ ሁሉም እኔ የገባኝ እንዲህ ነው በሚመስሉ መልኩ ለማስረዳት በመንግስት በተዘጋጀው በራሪ ወረቀት ላይ አንገታቸውን ደፍተዋል:: ከሌላኛው በቡድን ሆነው ከቆሙት መሀከል ደግሞ በዚህ ጉዳይ ብቻ ከስራ ላይ የመጣ የሆነና እዚህ ሶስት ቀናቶችን እንዳሳለፈና ነገር ግን አሁን ወደ ሥራም ለመመለስ እያመነታ መሆኑና ከሁለት ያጣ እንዳይሆን ስጋቱን ለቡድኑ አባላት ያጫውታቻዋል::
 እኔ ለብቻዬ ተነጥዬ ቆሜ ስለነበር በደብ በህዝቡ መሀል ያለውን ነገር መታዘብም ሆነ መመልከት እችል ነበር:: ቢገርማችሁም ባይገርማችሁም ከግማሽ በላይ ህዝብ ጋቢ፣ ሹራብና ካቦርት የለበሰ ነበር ታዲያ ይህ ምን ሊገርመኝ ወንድሜ እኮ 9: 00 ሰዓት ከለሊቱ ወጥቶ እኮ ነው 45ኛ ሆኖ የተመዘገበልኝ :: ይህ ህዝብ ደግሞ ወይ ስምንት ሰዓት ወይ ደግሞ ከዚያ በፊት ሊሆን ይችላል ከቤቱ የወጣው ::  ቤት ፍለጋ ከቤት ውጭ ማደር !
ይህን ትዝብቴን  እንድጭር ያስገደደኝን ዋና ጉዳይ  የሆነውን ዋና እርእሴን አልዘነጋውም። ይሄውላቹ ,,,ወጭ ወራጅ መኪና በዚያ ሲያልፍ ክላክስ ጥሩንባ ያሰማ ነበር :: ምክኒያቱም ጽሁፌን ስጀምር ጠቅሼላቹ ነበር የባንክ ቤቱና አስፋልቱን እርቀት በግምት 16 ሜትር ያህል ነው:: ታዲያ ስም ዝርዝራችንን ሲመዘግቡ መታወቂያችንን ሰብስበው ስለነበር ዕሮብ የተመዘገብነውን ሁሉ ለዓርብ እንድንመለስ ከነገሩን በኋላ መታወቂያችንን ለሶስት ግለሰቦች እንዲመልሱልን ሰጡዋቸው::
የእኔና የሌሎችን መታወቂያ የያዘው ግለ ሰብ መታወቂያችንን ሊመልስልን የሰበሰበን ከአስፋልቱ ጠርዝ ላይ ስለነበር ሰዎች ሲከቡት ሰዉ ከአስፋልቱ ላይ ወጥቶ ነበር:: ኤኬሌ,,, ኤኬሌ,,, ኤኬሌ,,,እያለና ግለሰቡ አቤት ሲል ሰጪው መልኩን ከመታወቂያ ላይ ካለ ፎቶ ጋር እያመሳሰለ ይመልስ ተያይዟል :: ታዲያ አንድ የከባድ መኪና (ሳኒዮ) የጥሩንባ ድምጽ የተሰበሰበውን ህዝብ አስደነበረው :: የመኪናው ጥሩንባ ድምጽ ከፍተኛ ስለነበር ሁሉም ሰው የስድብና የእርግማን ዓይነት ውርጅብኝ ያወርድበት ገባ::   ታዲያ ከዚያ ሁሉ ስድብ፣እርግማንና ከመኪናው ጥሩንባው ጩኧት ይልቅ ጆሮዬ የገባው ድምጽ አንድ አጠገቤ መታወቂያ ሊወስድ የቆመ ወጣት ድምጽ ነበር። አስቀያሚ ስድብ ,,,መቼም የስድብ ጥሩ ባይኖረውም ሹፌሩን አቦ እናትህ እንዲ ላድርግ ብሎ ሲሳደብ ነበር:: እኔ የምገባበት ጠፍቶኝ እንደመሸማቀቅ ብዬ አንገቴን ትከሻዬ ውስጥ ቀብሬ ቀና ስል አንድ እንደ እኔው ስድቡ ልቧን የሰበረባት መልከ መልከም ሴት ጋር ዓይን ለዓይን ተጋጨን :: ይህ ወጣት መጀመሪያ ዓመት የዩንቨርሲቲ የዶርም አባል የሆነውን ልጅ ትዝ እንዲለኝ አስደረገኝ :: ይህ የዶርም አባል የነበረው ልጅ አንድ ቀን FRESH MAN ገና እንደገባን እንዲህ ብሎ ስለሰደበኝ ብቻ ከግቢው በውጤቱ ማነስ (AD) ሆኖ እስከባረር ድረስ አንነጋገርም ነበር::
አቦ በእናታችሁ  ስለእናታችሁ ብላችሁ  እናት የብዙ ነገራችን ምሳሌ ነች እኮ
እ    እ  እ   እ    እ   ናት!
የ ጭንቋ የምጧ የእመሟ ድምጽ ናት::
አዲስ አበባ

ግንቦት 28፣2005 

Wednesday, June 12, 2013

የተጣጣፉት ሜኑዎች


አንዱን ቀን ከሁለት የቅርብ ወዳጆቼ ጋር ምግብ ቢጤ ፈላለግንና ወደ አንዱ ሆቴል ገባን፡፡

የምርጫችን ምክንያት “ትላንት የበላነው ቆንጆ ምግብ አለ...ዋጋውም መልካም ነው” የሚለው የገበታ ሸሪኮቼ ምክንያት ነው፡፡

ከመግባታችን ትላንት በላን...በ70 ብር ይሸጣል ያሉትን ምግብ አዘዝን፡፡

አስተናጋጁ ጠረጴዛውን አፀዳድቶ ሜኑ ይዞ ከተፍ አለ፡፡

“ፍሬንድ ነገርንህ እኮ” አለው አንዱ ከመካከላችን ፤ አስተናጋጁ ደግሞ “ወዳጄ የዋጋ ጭማሪ ስለተደረገ ትስማሙ እና አትስማሙ እንደው ብታዩት ይሻላል ብዬ ነው” አስረዳ፡፡

ሜኑው ተገለጠ፡፡ እንዳለቀ ሱሪ የተጣጣፈ ይበዛዋል፡፡

ትላንት 70 ብር ተበላች የተባለችው ምግብም ለመልስ እንዳታስቸግር ድፍን 100 ሆናለች፡፡

ጠላታችሁ ክው ይበል!

እኔም እንዲሁ ነው ድንግጥ ያልኩት፡፡ በአንድ ቀን አዳር? ጬሂ ጬሂ ያስብላል፡፡
ግን በየት በኩል? ማንን ደስ ይበለው ብዬ? ዋጥ ማድረግ እየተቻለ፡፡

“ለምን?” አልነው አስተናጋጁን፡፡

አስተናጋጁ የሚገባበት ጠፍቶት “ምንም አላውቅም፡፡ ትላንት ከሰአቱን እረፍት ነበርኩ ዛሬ ስመጣ ዋጋ ማስተካከያ እንደተደረገ ሰማሁ” አለ ቁልጭ ቁልጭ እያለ፡፡
የፈጣሪ ያለህ! ለማን አቤት ይባላል?

ያን ቤት በንዴት ብቻ ለቀን ወጣን፡፡ እኔ በበኩሌ በዛው ቀረሁ፡፡

ወዳጆቼ አሁን አሁን በአዲስ አበባ ካፌዎችና ምግብ ቤቶች ቋሚ የሚባል ነገር ጠፍቷል፡፡
ትላንት ያገኛችሁትን አገልግሎትና ዋጋ ዛሬ እንደሚያገኙ ርግጠኛ መሆን ለብዙ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ከብዷል፡፡

ሜኑዎቻቸው እንደ አየር ጠባዩ አሁንም አሁንም ይቀያየራል፡፡

ከምግብ ዝርዝሮች ፊት ለፊት ያሉት የዋጋ ተመኖች በቁርጥራጭ ወረቀቶች ተለጣጥፈው የቀድሞ ይዞታቸውን ለቀዋል፡፡

የንግድ ቤቶቹ ባለቤቶች ዋጋ ለመጨመር የሚወስድባቸው ፍጥነት በላስቲክ የለበጡትን ሜኔዎች በወጉ ለመቀየር እንኳ ጊዜ የሚሠጥ አይደለም፡፡

ታሸገው ከሚሸጡት ውሃና ለስላሳ ጀምሮ ምግብ ፣ ካፌ አፈራሽ መጠጡ ፣ሻይን ጨምሮ ሃገር አማን አይደለም እንዴ በሚያስብል ፍጥነት ያሻቅባሉ፡፡

ጭማሪው ደግሞ እስቲ ይሁና ለማለት እንኳ ትዕግስት አይሠጥም፡፡ ሊያውም መጠኑ እንዳለ ካለ፡፡

አንዳንዴ ትላንት ወይም በዚህ ሳምንት የበላሁት ነው፣አንዱ ሁለት ሰው አጥግቦ ይመልሳል ያሉትን ምግብ ወዳጆን ሊጋብዙ ሲሄዱ ከርሶ አንጀት እንኳ ጠብ የማትል ኪኒን የምታክል የምትሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ያሸማቅቃል!

እንዲህ ያለውን ድንገቴ የዋጋ ጭማሪ በካፌው ላይ አነሳን እንጂ በብዙ ምርትና አገልግሎት ላይ የሚታይ ነው፡፡
መቼም እንደ ዜጋ ሁሉኑም ማስደንገጡ ባይቀርም ጭንቁ የሚበዛው የወር ገቢው ተቆጥሮ ለምትሠጠውና እዚህጋ ዋጋ ጨምሬ ላካክስ በማይለው ቅጥር ሰራተኛ ላይ ነው፡፡

የቤት ኪራዩ ሲንር ወርሃዊ የትምህርት ቤት ክፍያው ሲጨምር ዶላር እዚህ ገባ እየተባለ ብጣሸ ጨርቅ ለመልበስ የወር ደሞዝን ሲገዳደር ታክሲም መንገድ ግንባታው አንድ መታጠፊያ ጨመረብኝ ብሎ ሳንቲም ለመመንተፍ ሲሯሯጥ  መቆጣጠር የሚገባው ቢሮ ተቀምጦ “ህገ ወጥ ነው፡፡ ያስቀጣል” ከማለት ባለፈ ህግን መጣስ እንደሚያስቀጣ ሳያሳይ ሲቀር ተጐጂው ይህው ግብሩን ያለ አንዳች ሽርፍራፊ የሚከፍለው ደሞዝተኛ ነው፡፡

ቀነስ ብሎ የሚገዛው ነገር ያጣ ሠው፣ ግሸበቱ ቀነሰ ወደ አንድ አሀዝ ወረደ 6 በመቶ ገባ ገለመሌ ቢባል ቁጥር እንጂ ምን ትርጉም ሊሠጠው ይችላል?

ምክንያቱ ላይ ደግሞ እናውራ

እኔ እኛ ተጠቃሚዎቹን ከመውቀስ እጀምራለሁ፡፡

ዘመናችን እራሱ የተወደደ ነገር ሁሉ ትክክልና የሚሻል የመሰለበት ነው፡፡
የልባችንን የሚያውቁት ነጋዴዎቹም ዋጋውን ሰማይ ሰቅለው የእቃውን ጥራት በዋጋው ውድነት እንድንለካው በማዘን ያስቀምጡልናል፡፡

አንድ ከፈረንሳይ የመጣ ወዳጄ የካፌ ቢዝነስ ያበላል ተብሎ የከፈተውን ሬስቶራንት ልመረቅ ገና በ4ኛ ቀኑ ሄጄ የሱም ሜኑዎች ተለጣጥፈው ሳይ ተገርምኩ፡፡ “አንተም?” ብለው፡፡
“ምን ላድርግ ብለሽ ነው ቀድሞ ብሎ የወጣውን ዋጋ ያዩ ጓደኞቼ ቤትህን ርካሽና መናኛ ያስመስለዋል በል ቆልለው በለውኝ ነው” ብሎኛል፡፡

ቀድሞ የነበረውን ወጪ እና ገቢውን አሰልቶ ያተርፈኛል ብሎ የወሠነውን ሒሳብም መቀየር ያስፈለገው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡  
በርግጥ አንድ ሰው የካፌና የምግብ ቤት አገልግሎት ልሰጥ ብሎ ስራ ሲጀምር የራሱ የሆነ ብዙ ወጪ አለው፡፡ የቤት ኪራይ ይከፍላል ሰራተኛ ይቀጥራል የጥሬ እቃ ወጪ ይጠብቀዋል፡፡ የመብራትና ውሃም ይቆርጣል… ሌላም ሌላም፤

ከነዚህ አገልግሎቶች የሚቀበለው ገንዘብ ግን በትክክል ለሚሠጠው አገልግሎት እና ለሚያገኘው ተገቢ ትርፍ ብቻ ነው ወይ? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡

መሸቶ በነጋ ቁጥር ለሚጨምረው ዋጋ መሸቶ ሲነጋ የቤት ኪራይ እየጨመረ? የመብራትና የውሃ ዋጋ እየናረ? ለሠራተኞቹ ደሞዝና ጉርሻ እንዲሁም ጥቅማጥቅም እየሠጠ? ወይስ ሌላ?

አንድ ኪሎ ቲማቲም በ5 ብር ሲጨምር በአንድ ምግብ 15 ብር ሚቆነድደን ነጋዴ  ሲቀንስስ ይቀንሳል እንዴ?

ለተጣጣፉት የአዲስ አበባ ሜኑዎች ምን ምክንያት አንስቶ ማሳመን ይችላል?


                       ቸር ያሰማን!



ጋዜጠኛ ሃኒ ሰለሞን ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቀዋል፡፡ አሁን በሸገር ኤፍ.ኤም ሬዲዮ በጋዜጠኝነት በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሃሳብና አስተያየት ካለዎት በኢሜላቸው honeysolomon123@yahoo.com በፌስቡክ ገጻቸው https://www.facebook.com/honey.solomon.3 ሊያገኟቸው ይችላሉ፡፡

Wednesday, June 5, 2013

ስሜን ያየ!

ዝም ብሎ መተራመስ ምንድነው?
የአዲስ አበባን ውሎ ማወቅ የፈለገ በስራ ቀን ቢሮ መግባቱን ትቶ አንዱ ኢንተርኔት ካፌ ጎራ ይበል፡፡ ለካ ስንት ነገር አምልጦኛልና የሚል ቁጭት ይፈጠርበታል፡፡ ትላንት ሰኞ ግንቦት 26 በእረፍት ስም ቢሮ ሳልገባ ብውል ሀገሪቱን እና ህዝቦቿን ስታዘባቸው ዋልኩ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከሳምንታት በፊት ባንክ ሄጄ መታወቂያዬን አዩና ሌላ የሚረባ መታወቂያ ካለሽ አምጪ ይሄኛው ሳይታደስ 2 ዓመት ያለፈበት ነው ተባልኩ፡፡ መቼ ወደ ቀበሌ መሄድ እንዳለብኝ የመከረኝ ደህና ዘመድ ስላልነበረኝ ከዛሬ የተሻለ ቀኝ አላገኝም አልኩና ሰኞ ወደ ከሰዓት በኋላ ከቤት ወጣሁ፡፡ አስቸኳይ  ፎቶ ተነሳሁ፡፡(‹አስቸኳይ ፎቶ አለ?› ተብለው ሲጠየቁ ‹አለ ግን ለዛሬ አይደርስም› የሚሉ ፎቶ ቤቶች አሉ ብለው ካሳቁኝ ሳምንት አልሞላውም፡፡ የኔው ከ35 ደቂቃ በኋላ የሚደርስ ነበር) እስከዛው ኢንተርኔት ካፌ ልቆይ ወሰንኩ፡፡ ቤቴ ለፎቶ ቤቱ ይቀርባል፡፡ ኢንተርኔት ካፌው ደግሞ ለፎቶ ቤቱ ይቀርባል፡፡ ከኢንተርኔት ካፌው በቅርብ ርቀት ላይ ውዱ ቀበሌአችን ይገኛል፡፡
ሳላስበው ለአንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ በኢንተርኔት ካፌው ስቆይ ሰዎች እየመጡ እንዲህ ይጠይቁ ነበር፡፡
‹ስሜን ታዩልኛላችሁ?›
< ፎቶ ኮፒ አለ?›
‹  መመሪያውን ታሳዩኛላችሁ?›
‹ፎቶ ኮፒ›
‹የኮንዶሚኒየም ምዝገባ ካርዴ ይኸው! ስሜ - - -›
ወጣት ሴቶች፣አሮጊቶች ሽማግሌዎች፣ጎልማሳ ወንዶች  - - - ከኢንተርኔት ጋር ትውውቅ የሌላቸው ግራ የገባቸው ዜጎች ኢንተርኔት ካፌዋን በስራ እና በጥያቄ ብዛት ወጥረዋታል፡፡ ሲያቀብጠኝ ብዙ ሊያቆየኝ የሚችል ኮፒ የሚደረግ ጉዳይም ይዤ ነበር የሄድኩት፡፡በየጣልቃው የቤት አዳኞቹን ፎቶ ኮፒ ስለምትሰራ ካሰብኩት ትንሽ አቆይቶኛል፡፡ በቃ ኮፒው እስኪያልቅ ፎቶዬን ይዤ ቀበሌ ደረስ ብዬ ልምጣ አልኩና ሄድኩ፡፡
ቀበሌው በሰው ብዛት ጢም ብሏል፡፡በፊት መታወቂያ  የሚታደሰው አዲስ በተገነባው የቀበሌው ፅህፈት ቤት ህንፃ ላይ ፤በአንድ መስኮት፤ 5 ደቂቃ ላልበለጠ ጊዜ በሚሰጥ አገልግሎት ነበር፡፡ አሁን ከፎቁ ወርደው በአንድ ነባር አሮጌ አዳራሽ ወርደዋል፡፡‹ወደ ህዝቡ ቀረብ እንዲሉ ነው› ብላ ቦታው የተለወጠበትን ግምቷን ያካፈለችኝ ሴት ነበረች፡፡ አዳራሹ ውስጥም ከአዳራሹ ውጪም ሰው እንደጤፍ ፈሷል፡፡
‹ምንድነው ይሄ ሁሉ ሰልፍ?› አልኩ
‹መታወቂያ  ለማሳደስ›
‹እስከዛሬ የት ከርመው ነበር?› አላልኩም፡፡ እኔ ራሴ የት ከርሜ ነበር?
የሰልፍ ቁጥር ደግሞ ይታደላል፡፡ 68 ሰዎች ቀድመውኛል፡፡ 69 ቁጥርን ተቀብዬ በማግስቱ ለመመለስ ቁጥር ወደሚሰጠው ሰው ሄጄ ስጠይቀው፡፡ ‹ቆይ ወረፋ ይዘሽ ጠብቂ የተሰጠው ቁጥር ሲያልቅ ነው አዲስ የምንሰጠው› አለ፡፡ ህዝቡን እንዳሻው ሲያደርገው አሳላፊው ፊት ላይ የነበረው ደስታ ልጁን የሚድር እንጂ መታወቂያ ለመውሰድ የመጣ ሰው የሚያሰልፍ አይመስልም፡፡ የቀበሌው ጊቢ ውስጥ ትዳር አለመያዛቸውን ለማስመስከር በሚሯሯጡ ሰዎችም ተሞልቷል፡፡ ‹እንደዚህ አይነት ሰርግና ምላሽ ውስጥ መቆየቱ አያዋጣኝም› አያልኩ በውስጤ እያልጎመጎምኩ ፤ግርግሩ እስኪበርድ ወደ ቀበሌ ድርሽ እንደማልል ለራሴ ቃል እየገባሁ ወደ ኢንተርኔት ካፌው ተመለስኩ፡፡
የኢንተርኔት ካፌው ባለቤትና የኔን ኮፒ እያደረገች የዛን ሁሉ ሰው ጥያቄ ስታስተናግድ የነበረች ልጅ በወሬ ጠመድኳት፡፡
‹እኔ የምልሽ ምንድነው ትርምሱ?›
‹10 በ90 እና 20 በ80 ቤት ለመመዝገብ የባንክ አካውንት ክፈቱ ተብሏል›
‹ታዲያ ስማችንን እዩልን የሚሉት ለምናቸው ነው?›
‹ ከዚህ በፊት ኮንደሚኒየም የተመዘገቡት ናቸው፡፡ ቢጫ ካርዷን ይዘው ይመጡና ስማችንን እዩልን ይላሉ፡፡ እሱ ዝርዝር ደግሞ እኛ ጋር አይገኝም፡፡›
‹የት ነው የሚገኘው?›
‹እኔጃ! እዛው ቤቶች ልማት ይሆናል፡፤ ኢንተርኔት ላይ መኖሩንም የነገረን የለም›
‹ለምንድነው ስማቸውን የሚፈልጉት?›
‹ይጠፋል አሉ›
‹ወዴት ይጠፋል?›
‹በቃ ይጠፋል፡፡ እልም እልም ብሎ ይጠፋል፡፤የእኔ እህት አሁን ከተመዘገበችበት ስሟ ጠፍቷል፡፡ እንዳትከስ ደግሞ ቢጫ ካርዷን አጣችው›
‹ታዲያ የአዲሱ ምዝገባ ዕለት እዛው ሄደው ጠይቀው ጠፍቶ ካገኙት ከመንግስት ጋር አይነጋገሩም እንዴ?›
‹ እኔ ምን አውቃለሁ ሰው ዝም ብሎ መተራመስ ይወዳል፡፡ አሁን ቅድም የመጣቸውን ሴትዮ አይተሻታል? ጠዋት 3 ሰዓት ላይ ስሟን ፍለጋ ስራ አቁማ ከቢሮ የወጣች እስካሁን ሳታገኘው ይሄው 9 ሰዓት ሆነባት፡፡ ተይ ስምሽን ኢንተርኔት ካፌ አታገኚውም ብንላት የቤት ዕጣዋን የወሰድንባት ይመስል እንደጠላት አየችን፡፡ ደግሞ ለዛ ውሀ ላይ እየተተከለ ለሚሰምጥ ቤት፡፡ ሁለት ኮንደሚኒየም እኮ ሰምጧል አልሰማሽም?››
‹ከሰማሁ ቆይቻለሁ፡፡ ግን እኔ ዘንበል እንዳለ ነው የቆምኩት መስመጡን አልነገሩኝም፡፡ - - -እኔ የምለው ግን ፤እናንተ ዛሬ ስራ የበዛባችሁ ምን እየሰራችሁ ነው?›
‹የባንኩን ፎርም እና መታወቂያ ፎቶ ኮፒ እናደርጋለን፡፡ መመሪያው ደግሞ ፋና ዌብሳይት ላይ አለ እሱን እናሳያለን፡፡ምን እንደሚያስፈልግ ዌብሳይቱ ላይ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል፡፡ እሱን ቢያዩኮ መቼ መምጣት እንዳለባቸው ስለሚያውቁ ግርግሩም ትንሽ ቀነስ ይል ነበር፡፡ለምሳሌ የ40በ 60 ምዝገባ ገና ነሀሴ ላይ ነው፡፡ ሰው ግን ግርግርና መንሰፍሰፍ ይወዳል፡፡›አለችኝ እንግፍግፍ እያለች፡፡
‹እስኪ ለኔም አሳዩኝ› አልኳት፡፡ አንዱ የኮምፒውተር ስክሪን ፊት አስቀመጠችኝ፡፡ ለነባር(ከዚህ በፊት ኮንደሚኒየም ዕጣ ላይ ለመግባት ለተመዘገቡት) እና  ለአዲሶች ተብሎ ተለይቷል፡፡ አዲስ ተመዝጋቢ ሲኮን በየወሩ የሚቀመጠው ተቀማጭ ከነባሮቹ ይቀንሳል፡፡ ቀደም ብዬ የሰማሁት ቢሆንም የኢንተርኔት ቤቷ ልጅ የተረዳችውን እንድትነግረኝ ጠየቅኳት፡፡
‹መዋጮው ለአዲሶቹ የሚቀንሰው የቤቱ ዕጣ በቶሎ ስለማይደርሳቸው ነው፡፡ 7 ዓመት መጠበቅ አለባቸው፡፡ አዲሶቹ  በሚያስቀምጡት ብር ነው ለነባሮቹ ቤት የሚሰራው፡፡ ነባሮቹ የዛሬ 5 ዓመት የቤት ባለቤት ይሆናሉ፡፡ ነባሮቹ ልክ ቤታቸው እንደገቡ ደግሞ በሚከፍሉት ብር ለአዲሶቹ ቤት ይሰራላቸዋል፡፡›
‹ነባሮቹ ቤታቸውን ከተረከቡ በኋላ ለምን ይከፍላሉ አስቀመጡ አይደል እንዴ 5 ዓመት ሙሉ?› አላዋቂነቴ ሳይገርማት አልቀረም
‹እንደ ተቀማጩ እኮ 50 ፐርሰንት ነው፡፡ የት ነበርሽ አንቺ ይሄ ሁሉ ሲወራ?›
ምሳ ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ቴሌቪዥን ለነባር ተመዝጋቢዎች ፣ ለሴቶች ለመንግስት ሠራተኞች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ሰምቻለሁ፡፡ እንዲህ እያወራን አንድ ሰውዬ መጣ፡፡ ‹እስኪ የኮንደሚኒየም ዕጣ እዩልኝ› አለ፡፡ፊቱ በደስታ በርቷል፡፡
‹አዲስ የኮንደሚኒየም ቤት እጣ አለ እንዴ?› አልኩ መቼም መጠየቄ ካልቀረ የሚሰራ የሚወራውን ሁሉ ልወቅ የሚል ዘመቻ የያዝኩ ይመስላል፡፡
‹በመጨረሻ የወጣው ነዋ›
‹መቼነው እሱ የወጣው? ይቅርታ ከዚህ በፊት ስላልተመዘገብኩ ዕጣ ሲወጣ ጉዳዬ ብዬ አልከታተልም ፡፡› አልኳት፡፡
‹ያኔ ነዋ የምርጫው ሰሞን?›
‹የቱ ምርጫ?›
‹የኢህአዴግ ምርጫ ነዋ! ልክ ምርጫው ሲቀርብ እኮ ነው የወጣው› አለች
‹እኮ ታዲያ እሱ ዕጣ አልቆየም እንዴ?›አልኩና ከጨዋታ ውጪ መሆኔን ለመሸፈን ዕጣው እንዲታይለት የፈለገውን ሰው ወደ ጨዋታው እንዲህ ስል አስገባሁት፡፡
‹አንተ እስከዛሬ እንዴት ዕጣውን ሳታይ ቆየህ?›
‹ሰዎች የኮንደሚኒየም ዕጣ እንደደረሰኝ ነግረውኝ፡፡አላምን ብዬ አይቼው አሁንም በድጋሚ ኢንተርኔት ቤት ቀይሬ ላየው ነው፡፡›
‹እንኳን ደስ ያለህ፡ ግን ለምንድነው ደጋግመህ የምታየው ዕታ ከወጣ በኋላም ስም ይጠፋል?›
‹ሳይሆን እኔ አልተመዘገብኩም ነበራ!›
‹ምን?!›
‹ሙች! ለሴት ቅድሚያ ይሰጣል ብለን ሚስቴ ነበረች የተመዘገበችው፡፡ ሁልጊዜ ዕጣ ሲወጣ የሷን ስም ነው የምንፈልገው፡፡ አሁን እኔን ደረሰህ አሉኝ ስሜ እስከነ አያቴ እስከ አድራሻዬ እኮ ነው ቁልጭ ብሎ የተገኘው፡፡ምንም ስህተት የለበት፡፡›
‹ቢጫዋ ካርድ አለችህ?›
‹የለችኝም፡፡ አልተመዘገብኩም እያልኩሽ?›
‹ሌላ ሰው ተመዝግቦልህ ይሆናል፡፡›
‹ማንም አልተመዘገበልኝ፡፡ ደግሞስ ለሰው መመዝገብ ይቻል ነበር እንዴ?›
‹ታዲያ እንዴት ሊደርስህ ይችላል? ወይ የሆነ የሄድክበት አቋራጭ መንገድ ይኖራል፡፡›
መሀላውን ደረደረ፡፡ እኔ ጭንቅላት ውስጥም እንዲህ እንዲህ እያሉ ጥያቄዎች ተደረደሩ፡፡ ሰዎች የሆነ የሰሙት ነገር ሳይኖር መቼም ስማቸውን ፍለጋ ኢንተርኔት ቤት ለኢንተርኔት ቤት አይንከራተቱም? የኮንደሚኒየም ተመዝጋቢዎች ስም በኢንተርኔት ላይ ይገኛል አይገኝም? ሰዎች ተመዝግበን ስናበቃ ስማችን እየተሰረዘ ጠፋ እያሉ ይጨነቃሉ፡፡ እውነት ነው ውሸት? መቼም ላም ባልዋለበት ኩበት አይለቀምም እሳት በሌለበትም ጭስ የለም፡፡ አንድ ሰው ሳይመዘገብ የኮንደሚኒየም ዕጣ የሚደርሰው እንዴት ባለው ተዓምር ነው? ተመዝግቦ 10 ዓመት ቤት ከመጠበቅና ሳይመዘገቡ ተዓምር ከመጠበቅ የቱ ያዋጣል? እሺ መንግስት ራሴ ሰርቼ ነው የምሰጣችሁ ብሩን ለኔ ስጡኝ ከዛ ዕድሜ ዘመናችሁን ቤት እያላችሁ ጠብቁኝ ማለቱን ይበል የሚሰለፍለት ካገኘ እሰየው፡፡ ግን ሰፋ ያለ የመመዝገቢያ ጊዜ ገደብ መስጠት(ልክ የምርጫ ካርድ እንደመውሰድ ያለ በጠዋት ቤት ለቤት እየዞሩ ‹የመጨረሻው ቀን ቀርቧል› እያሉ እንደሚቀሰቅሱት ዓይነት)፣ከምር ቤት የቸገረውን ለይቶ መስጠት፣መሬት ሰጥቶ እንደፈለጋችሁ ስሩ ማለት አይችልም ነበር?
‹አንቺ ግን እንደባለፈው እንዳያመልጥሽ አሁን ተመዝገቢ፡፡በኋላ እንዳይቆጭሽ፡፡› አለችኝ ስወጣ ጠብቃ

እኔ ለራሴ ገና ጥያቄ ላይ ነኝ፡፡ ብር ብሎ ተነስቶ እንደሚሰለፍ ህዝብ ብዙ ነገር አልገባኝም፡፡ ጥያቄ - ጥያቄ  -ጥያቄ ፡፡ ጥያቄ አያልቅም፡፡



ጸሃፌ ተውኔት መዓዛ ወርቁን በሸገር የአልጋ በአልጋ ተከታታይ ድራማና በህይወት መሰናዶ ድራማ ደራሲነታቸው እናስታውሳቸዋለን፡፡ አሁን እየታየ የሚገኝ ዝነኞቹ የተሰኘ ቴአትርም አላቸው፡፡ አስተያየት ካላችሁ በፌስቡክ አድራሻቸው በኩል በhttps://www.facebook.com/meaza.worku.39 ሊያገኙዋቸው ይችላሉ፡፡