Total Pageviews

Friday, May 3, 2013

ለማንነታችን መገለጫዎች ክብር እንስጥ!!!



እኛ ኢትዮጵያውያን ከአለም በዚህ ነገር አንደኛ ምንናም እያልን የምንኮፈስባቸው ብዙ መገለጫዎች ያሉን ህዝቦች ነን፡፡ የአለም ህዝብ በአድናቆት ያጨበጨበላቸው የጥንት ስልጣኔዎቻችን አሻራ ያረፈባቸው አክሱም፤ላሊበ፤ነጃሺ መስጊድና የመሳሰሉት፡፡በብዝሀ ህይወት ሀብታቸው የአለም ቁንጮ ያደረጉን እን ሰሜን ፣አዋሽ ፤ባሌ ተራሮች ፤ኦሞ ፤ነጭሳርና ጋምቤላ ብሄራዊ ፓርኮቻችን እና በውስጣቸው የሚገኙት እነ ዋልያ፤ቀይ ቀበሮ፤ሳላህ፤ኒያላ የመሳሰሉት ብርቅዬ እንስሳት፤የቱሪስት መንጋጊያ የሆኑት እነ አዋሳ ፤ጣና ፤ላንጋኖ፤ሻላ እና አቢያታ ሀይቆቻችን በእርዝመታቸው በአለም ከሚጠቀሱ ወንዞች መካከል እነ አባይ፤ባሮ፤አዋሽ፤ጊቤ፤ዋቢ ሸበሌ የመሳሰሉት ታሪክ ሲያወሳቸው የኖሩት የነገስታቶቻችንና የፈላስፎቻችን ስሞች እነ ሚንሊክ፤ቴዎድሮስ፤፤ምንትዋብ፤ካሌብ፤ዘረያቆብና ሱሲኒዮስ፡፡
የአለም ዝቅተኛው ስፍራ ዳሎል ፤ኤርታሌ ፤የሉሲ መገኛ ሃዳር …..እረ ስንቶቹ ተጠቅሰው ያቻላል፡፡በዘፈን የምናውቃቸው እነ ባቲ፤አምባሰል ፤መቅደላ፤ገራዶ፤…እነዚህ ሁሉ ድንቅ ስሞች በሞሉባት ሀገር ….Network café, Dallas café, Denver, lime tree café, Boston day Spa, Jolly bar, purple café, liquid lounge, flirt lounge, platinum, H20, Faranite, Stockholm, Amsterdam…እረ መአት አሉ ፤(እነ ሱባ ላውንጅ ፤እን ጃዝ አምባ፤እነ ቃተኛ፤እንጎቻ ፤ላሊበላ ፤እክሱም ሬስቶራንቶች ፤ሙልሙል ዳቦ የመሳሉትን ስያሜዎች ሳላደንቅ አላልፍም )፡፡
እረ ግን ምነው የኛ ስሞች የማይመጥኑ ሆነው ነው?....ወይስ??? በጣም የሚገረመኝ ደግሞ የባህላዊ እቃ መሸጫዎቻችን ስያሜዎች ናቸው …ፕሪቲይ ጥበብ፤ፐርፌክት የባህል ልብሶች መሸጫ፤ቴክሳስ የባህል እቃዎች ምናምን (እነ እቴጌ ጥበብ፤ጋሙ የባህል ልብስ ፤አምባሰል የመሳሉትን አሁንም ሳላደንቅ አላልፍም)፡፡
የባሰ የሚገርመውና የሚያሳፍረው ነገር ደግሞ …የፊልሞቻችን ነው፡፡በአማርኛ ፊልም ሰርቶ ርዕስ በእንግሊዘኛ እስቲ አሁን ምን ይሉታል ????... ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል(መቼም ተሰልፌ ባላያቸውም ተዋንያኖቹ ሀበሾች ስለሆኑና “ምርጥ የአማርኛ ፊልም” ብሎ ከሚጀምረው ማስታወቂያቸው የአማርኛ ፊልም መሆናቸውን አልጠራጠርም) City boy, Mr X, FBI, Honeymoon, Surprise, Made in China…ደሞ አሉ እንጂ shefu, mechaniku (ወይ ሙሉ በሙሉ እንግለዘኛ አልሆኑ ወይ አማርኛ አልሆኑ በቃ ጉራማይሌ ) እረ እንደው ስንቱ ተጠርቶ ስንቱ ይተዋል፡፡ እስቲ አሁን ከሀኒሙን እና ከጫጉላ የትኛው ያምራል??? ከሲቲ ቦይዝና ከከተማ ልጆችስ???...ፍርዱን ለናንተው፡፡
ለልጆቻችን እያወጣን ያለው ስምስ …Nancy, Barabara, Robert, Terry, Obama, mattew ምናምን??? እናትና አባቶቻቸው thank you, still, stupid ከሚሉት ከአስር ያልበለጡ እንግሊዘኛ ቃላት ውጪ የማይችሉ ህጻናት እንግሊዘኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እስኪመስል ድረስ አማርኛ እየረሱ ነው ....ይሄስ ምን ይሉታል???  አማርኛ መናገር የሚያስቀጣባቸው ት/ቤቶችስ እንዳሉ ታውቃላቸውሁ? እንዴታ እንኳን እኛ መንግስትም ያውቃል አትሉኝም፡፡
እንደው ለነገሩ እነዚህን ጠቃቀስኩ እንጂ ስንት አለ እኮ በየመንደሩ ኦባማ በለጬ፤ቦልት በለጬ፤ አርሰናል አወዳይ፤ ኦፕራ ምርጥ የጉራጌ ጫት ምናምን ጉድ እኮ ነው እነ ኦባማ፣ ቦልትንና ኦፕራን የመሳሰሉ የአለም እንቁዎች ለጫት መጠሪያነት ??? አንዱ ምን እንዳለኝ ታውቃለችሁ፡፡እነዚህን ስሞች እኮ የሚሰየሙት ቃሚዎቹ ቅመው እንደነሱ እንዲያስቡ ነው፡፡ባለ መቶው ቦልት በለጬ ደግሞ አለኝ ከ9 ሰከንድ ባነሰ ያመረቅናል(ቦልት መቶ ሜትሩን ከ 9 ሰከንድ በታች እንደገባው ማለት ነው) ጉድ አኮ ነው!!
ዳላስ እንጀራ ፤ካሊፎርኒያ ድፎ ዳቦ፤ሎስአንጀለስ በርበሬ፤ቤጂንግ ቁርጥ ቤት፤ሎንደን ጠላ ቤት ፤ዲሲ ባልትና የሚሉ ስያሜዎች በቅርቡ ማንበባችን አይቀርም፡፡እስካሁን ላለመኖራቸውም እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
ጓዶች አማርኛችን ሀብታም እኮ ነው፡፡ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በኛ ብቸኛ ፊደል ይኮራሉ እኮ፡፡ታዲያ እኛ ወዴት እየሄድን ነው? ለነገሩማ መሪዎቻችንስ አሻራ የምትል ጥፍጥ ያለች አማረኛ ቃል እያለች (legacy), በለውጥ ፋንታ (transformation) እያሉ የሚያደነቁሩን፡፡ በሌላውማ እንዴት ይፈረዳል፡፡
ለነዚህ የአሰያየም ችግሮች ሰዎች የተለያዩ ምክንያቶችን ያቀርባሉ፡፡የወጣቱን ትኩረት ለመሳብ ፤የውጪ ዜጎችን ቀልብ ለመስረቅ የመሳሰሉት ፡፡እንደ እኔ ግን ወጣቱን የራሱን ባህል ፤ማንነትና  ብሄራዊ ስሜቱን ትቶ የውጪ ባህል ናፋቂ እንዲሆን እያደረግን ነው ትኩረቱን የምንስበው? ኧረ ጥሩ አድርገን ከሰራነው እኮ የወጣቱንም ሆነ የውጪ ጎብኚዎችን የምንስብባቸው ስንት ነገሮች አሉን፡፡በጃሉድ “የእርግብ አሞራ” ያልጨፈረ ወጣት አለ እንዴ? የእርግብ አሞራ እኮ ባህላዊ የህዝብ ዘፈን ነው፡፡ አሪፍ አርጎ ስለሰራው ግን የወጣቱን ቀልብ መሳብ ችሏል፡፡
ያደጉት ሀገራት ያደጉት እና እዚህ የደረሱት እኮ የራሱን ትቶ የሰው ናፋቂ የሆነ ትውልድን ይዘው አይደለም፡፡ይልቁኑንስ ለባህላቸው ፤ለማንነታቸውና ለብሄራዊ ስሜታቸው ክብር ሠጥተው እንጂ፡፡ ታዲያ እኛስ ክብር የምንሰጠው ነገር የለንም ወይስ???.... ጎበዝ እናንተው ፍረዱት!







kuku. A eb እዚሁ ፌስቡክ ላይ በመጻፍ ይታወቃሉ! በሙያቸው ጠበቃ ሲሆኑ የሚያነሷቸውን ማህራዊ ሃሳቦች የሚተቹበት ገጽ አላቸው….እነሆ አድራሻው!  https://www.facebook.com/kuku.eb ኢሜላቸውን ከፈለጉም እነሆ! kuku.eb@facebook.com

No comments:

Post a Comment