Total Pageviews

Saturday, May 11, 2013

የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ኢንተርኔት




ዓለም ከ50 ዓመታት በኋላ እንዴት ትሆን?..ይሄ ገሎበላይዜሽን (Globalization) አሁን የምናውቃትን ዓለም የፈጠረውን የዘር፣ የቋንቋ፣ የባህልና ምናልባትም የቀለም ልዩነቶች እያደበዘዛቸው ነው፡፡ በአንጻሩም የአንድ ዓለም…የአንድ ህዝብ…የአንድ ባህል ፍልስፍና እየጠነከረና እየደመቀ ነው፡፡ ይኼም በየቀኑ ኢንተርኔት ስጎለጉል ይበልጥ ይታየኛል፡፡ ኢንተርኔት ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል በእንግሊዘኛ ተጀምሮ አሁን ላይ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች እየተስፋፋ ቢመጣም አሁንም በ 'ሌሎች' ቋንቋዎችና በእንግሊዘኛ መሃል ያለው የመጠን ልዩነት ግዙፍ ነው፡፡ በመላው ዓለም ከሚነገሩ 6000 በላይ ቋንቋዎች እንግሊዘኛ የአንበሳውን ድርሻ ይዟል በኢንተርኔት፡፡ ለነገሩ መጀመሪያ እኒህ ከ6000 የበለጡ የንግግር ቋንቋዎች የጽሁፍም ቋንቋዎች አለመሆናቸውን ልብ ማለት ያሻል፡፡ ራሳቸው የቋንቋ ባለሙያዎችም ቢሆኑ በቁጥሩ ዙሪያ የተስማሙበት አይደለም፡፡ ይሁንና እኛ ለጨዋታችን እንዲረዳን ከ6000 ቋንቋዎች ግማሹ ያህል የጽሁፍ ቋንቋም ናቸው ብለን እናስብ፡፡ በነገራችን ላይ አንድ ቋንቋ የጽሁፍም ለመሆን የግድ የራሱ ፊደላት እንዲኖሩት አያስፈልግም፡፡ ለምሳሌ ከሃገራችን እንኳ የላቲን ፊደላትን የሚጠቀሙትን የኦሮምኛ እና የሶማሊኛ ቋንቋዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ወደ ኢንተርኔታችን እንመለስ፡፡ ከነዚህ ከ3000 ሺ የበለጡ  ቋንቋዎች እንግሊዘኛ 57 በመቶ ያህሉን ድርሻ ይዟል፡፡ ከዚህ የተረፈውን ደግሞ ራሺያን፣ ጀርመን፣ ስፓኒሽ፣ ቻይኒዝ፣ ፍሬንች፣ ጃፕኒዝ…እያልን መቀጠል እንችላለን፡፡ ቀጥለን ቀጥለን ግን 2900 በላይ የአለም ቋንቋዎች ከ0.1 በመቶ በታች ድርሻ ነው ያላቸው በኢንተርኔት ውስጥ፡፡ ከነዚህ መሃል አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግረኛና ሌሎችም የሃገራችን ቋንቋዎች ይገኛሉ፡፡ ይህ የእንግሊዘኛ ገንኖ መውጣት አሁን አሁን ላይ እየቀነሰ እየመጣ ቢሆንም ያለው ድርሻ ግን እንዲሁ በቀላሉ የሚነጠቅ አይሆንም፡፡ 
የአለም ቋንቋዎችና ኢንተርኔት - ከዊኪፒዲያ የተወሰደ



እንደ http://www.internetworldstats.com (http://www.internetworldstats.com/stats7.htm) ከሆነ የእንግሊዘኛ ተናጋሪዎች በ10 ዓመታት ማለትም ከ2000 የፈረንጅኛው የዘመን ቆጠራ እስከ 2011 ድረስ ያሳዩት ኢንተርኔትን የመጠቀም እድገት ያን ያህል የሚጋነን ባይሆንም ቋንቋው በኢንተርኔት ውስጥ ያለው መጠን አሁንም እያደገ ነው፡፡ ሃገሮች ምንም እንኳ ብሄራዊ ቋንቋቸው እንግሊዘኛ ባይሆንም የሚፈጥሩት ድረገጽ ግን እንግሊዘኛ ነው፡፡ በሃገራችን የሚገኙትን ትልልቅ የምንላቸውን ድረገጾች ብናይ እውነቱ ግልጽ ይሆናል፡፡ www.shegerfm.com , www.diretube.com, www.ethiotelecom.et (በተለይ ይኼኛው ሁለቱንም ቋንቋዎች ቢይዝም የመነሻ (default language)ግን እንግሊዘኛ ነው፡፡) www.nazret.com, www.ezega.com , www.ethiopianreview.com , www.tadias.com ፣ www.2merkato.com. እነዚህ ድረገጾች በዋነኝነት የተመሰረቱት ለኢትዮጵያውያን ሆኖ…አማርኛም የሃገሪቱ ብሄራዊ ቋንቋ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ…የምናገኛቸው በእንግሊዘኛ መሆኑ አስገራሚ ይመስላል፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ የመንግስት ድረገጾችን ብናይ  በአብዛኛው በተለይ አሁን አሁን አማርኛ የመነሻ (default language) እየሆነ ነው፡፡ ድረገጾቹ አማርኛን በመነሻነት ይዘው ትግረኛን፣ ኦሮምኛን እና እንግሊዘኛ ቅጂዎችንም አቅፈዋል፡፡ ለምሳሌ http://www.ethiopia.gov.ethttp://www.moe.gov.et, http://www.mofed.gov.et, http://www.moh.gov.et መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከነዚህ ውጭ በመነሻነት እንግሊዘኛን የሚጠቀሙ የመንግስት ድረገጾችም አሉ ከነዚህ ውስጥ http://www.tourismethiopia.gov.et, ዋነኛው ነው፡፡ ከመንግስት ድረገጾች ውጭ የዜና ፖርታሎች ለምሳሌ አዲስ አድማስ እና ሪፖርተር ጋዜጣዎችም በአማርኛ የተዘጋጀ ድረገጽ አላቸው፡፡ ይህ በሃገር ውስጥ ያለውን ሁኔታ ሲያሳይ ከውጭ ሃገር ድረገጾች በጣም ትኩረቴን የሳበውን ላጫውታችሁ፡፡ ሁላችንም የምናውቀው የኢንተርኔት ኢንሳይክሎፒዲያ www.wikipedia.org በአማርኛ ከ10 ሺ በላይ ጽሁፎችን ይዟል፡፡ ምናልባትም ይህ ቁጥር በአጠቃላይ በሃገር ውስጥ ያለውን የአማርኛ የኢንተርኔት ጽሁፍ መጠን ሳይበልጥ አይቀርም፡፡ በአፋን ኦሮሞና ትግረኛ ከመቶ በላይ ጽሁፎች ይገኛሉ፡፡ከዚህ ሌላ ዊንዶውስ 7ና 8 ከማይክሮሶፍት ካምፓኒ፣ አብዛኞቹ የመሰረተ-ሊነክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተሞች  ለአማርኛንና ኦሮምኛን ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ ኡቡንቱ ኦፕሪቲንግ ሲስተም ኮምፒውተራችንን በአማርኛ እንድንጠቀም ያስችለናል፡፡ ኧረ እነ ጉግልም የአማርኛ ሰርች ገጽ አላቸው፡፡ ይሁንና አብዛኛው ኢንተርኔትን በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የመጠቀም እድሉን እያመቻቹ ያሉት ግን ሃገር ውስጥ ያለነው ወይንም ጉዳዩ በጣም የሚመለከተን አካላት አይደለንም፡፡ ወይ የንግድ ድርጅቶች ወይም ለትርፍ ያልተቋቋሙ እንደ ዊኪፒዲያ ያሉት ናቸው፡፡ በሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መረጃ ከኢንተርኔት ላይ የማግኘት ነገርንማ አናስበው፡፡ ጠቅላላ መረጃን በተመለከተ አሁን ያለው የሃገራችን ቋንቋዎች ተሳትፎ ብዙም የሚያወላዳ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ማን ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ግልጽ አለመሆኑ አሳሳቢ ነው፡፡ በሌሎች ሃገራት ለምሳሌ በስፔንና በስፓኒሽ ተናጋሪ ሃገራት እንዲሁም በፊሊፒንስ ቋንቋቸው በተለይ በኢንተርኔት ላይ ያለው ምልክት አነስተኛ መሆኑ አሳስቧቸው የተቋቋሙ ማህበራት ይገኛሉ፡፡ በአማርኛ ማንበብ ብቻ ሳይሆን በተመቻቸ ሁኔታ ኢንተርኔት ላይ በአማርኛ መጻፍን መጀመር አለብን፡፡ ለዚህም የአይቲ ባለሙያዎች ሃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ ሌላ በዚሁ በኢንተርኔት ውስጥ የኢትዮጵያውያን ጥበብና እውቀት በአግባቡ አለመወከሉም ሊያሳስበን ይገባል፡፡ የአለምን ታሪክ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያንም ታሪክ ከኢንተርኔት በአማርኛ ማግኘት ያስፈልገናል፡፡ ዜናና መረጃ ብቻ ሳይሆን ሂሳብን፣ ሳይንስንና መማሪያ ጽሁፎች በአማርኛ ልናገኝ መብታችን፣ ይህንኑ ማመቻቸትና ለትውልድ ማስተላለፍ ሃላፊነታችንም ነው፡፡ ያለበለዚያ ታሪካችን፣ ባህላችንና ማንነታችን በቀላሉ ይዋጣል፡፡አንዳንድ የቋንቋ ባለሙያዎች ከአለም ቋንቋዎች ግማሹ ያህል በ2050 ይጠፋሉ ብለው ያምናሉ፡፡ መጀመሪያም ይህ የነበረ ችግር ቢሆንም ኢንተርኔት ደግሞ ነዳጁን አርከፍክፎበታል፡፡ ስለዚህ ከመንግስትም ሆነ ከመንግስት ውጭ የሃገራችን ቋንቋዎች ትኩረት ይሰጣቸው! ለዚህ የመረጃ ዘመን ይብቁ እላለሁ፡፡ ሳምንት መፍትሄ የምለውን ይዤ እመጣለሁ፡፡ 
ጸሃፊው ፌሩዝ ጀማል በሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 ሬዲዮ በ IT, ድምጽ ላይብረሪና ፕሮግራም ትራፊክ ሃላፊነት ይሰራሉ፡፡ ጸሃፊውን ለማግኘት በፌስ ቡክ ገጻቸው https://www.facebook.com/feraj?ref=tn_tnmn  በኢሜላቸው feruzj30@gmail.com መጠቀም ይቻላል፡፡

2 comments:

  1. Hule yemiyangebegbegn neger new, bizu hageroch smart phones quanquachewn endiyakatetu siyadergu yegna gin hi bay ata. Ahun rasu i am writing Amharic with English letters, how annoying

    ReplyDelete
    Replies
    1. yes sir....we need to create a way to use Amharic on the web easily. or else, we killing our identity.

      Delete