Total Pageviews

Saturday, May 18, 2013

የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ኢንተርኔት ፪


ያለፈው ሳምንት ያነሳሁት ሃሳብ ዛሬም ይቀጥላል፡፡ ኢንተርኔትና የሃገራችን ቋንቋዎች ያላቸው ግንኙነት በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ምናልባትም ነገ ተነገወዲያ ሃገሪቱን ከፍ ያለ ዋጋ ሊያስከፍላት ይችላል፡፡ እኛም ነጋ ጠባ ቋንቋችን፣ የራሳችን የመጻፊያ ሆሄያት ያሉን ማለታችንን ብቻ ሳይሆን ይህንን ከትውልድ የወረስነውን ማንነታችንን ጠብቀንና ቢቻልም አዳብረን ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባናል፡፡ ለሀለተኛው ሳምንት ጽሁፌ ስጎሎጉል አንድ ድረ ገጽ አገኘሁ፡፡ ሃገሮች በተለይ በዊኪፒዲያ የእውቀት ባህር ውስጥ የተወከሉበትንና የወከላቸውን ቋንቋዎች ያሳያል፡፡ ካርታውን ከዚህ በታች አድርጌላችኋለሁ፡፡

የራሷ ቋንቋ እና የመጻፊያ ፊደላት ያላት ሃገራችን የተወከለችው በእንግሊዘኛ አንባቢነት ነው፡፡ ምንም እንኳ በዛው ዊኪፒዲያ በአማርኛ ከ10 ሺ በላይ ጽሁፎች ቢኖሩም ሰዎች ለማንበብ የሚሄዱት እንግሊዘኛውን ቅጂ ነው፡፡ አንዳንዴ የሃገራችንን ሰው ታሪክ እንኳ ለማንበብ እንግሊዘኛው እየቀናን ነው፡፡ ይህ በርግጥ በአማርኛ የሚገኙት  ጽሁፎች  እንደ እንግሊዘኛው ቅጅ ሁሉ የተሟላና ዝርዝር አለመሆናቸው ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲሆን ማድረግ ግን የኛው ጥረትና ሃላፊነት ነው፡፡ አንዳንዴ ቅኝ ከተገዙ ሃገራት ምን እንደሚለየን አስብና የሚለየን ነገር አለመኖሩ ቢኖር እንኳ የክር ያህል የቀጠነ መሆኑ ይታየኛል፡፡እስቲ ሁለት የዊኪፒዲያ ጽሁፎችን  እናነጻጽር፡፡ የመረጥኩት ራሱ አማርኛን ነው፡፡ ይኸው እንግሊዘኛው...http://en.wikipedia.org/wiki/Amharic_language የአማርኛው ደግሞ ይኸው...http://am.wikipedia.org/wiki/%E1%8A%A0%E1%88%9B%E1%88%AD%E1%8A%9B    በሁለቱ የአንድ ጽሁፎች ሁለት ቅጅዎች ማካከል ያለው ልዩነት የትየለሌ ነው፡፡የእንግሊዘኛው ቅጅ የተሟላ የግስና ሌሎችም ቴክኒካዊ ስርዓቶችን ሁሉ ሲያሳይ አማርኛው ግን የሚያሳየው ታሪካዊ አመጣጡን ብቻ እርሱም አስር መስመር በማይሞላ አንቀጽ ፡፡ የሌሎች ሃገራት ልምድ የሚያሳየው ይህንን መቀየር ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የስፓኒሽን የዊኪፒዲያ ታሪክ ብናይ...የስፓኒሽ ዊኪፒዲያ ያኔ ገና በመጀመሪያዎቹ ጨቅላ ዓመታት ላይ ከዊኪፒዲያ ተገንጥሎ ወጥቶ የራሱን ድረገጽ ከፍቶ አሁን ላይ ከዋናዎቹ የኢንተርኔት የመረጃ ምንጭ ሆኖ ይገኛል ለቋንቋው ተናጋሪዎች፡፡  ከዚህ ሌላ እኔ በግሌ ያስደነቀኝ በስፔን የሚገኘውና በካታላን ህዝቦች የሚነገረው የካታላን ቋንቋ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቋንቋ የበለጠ የጽሁፍ መጠን በዊኪፒዲያ ላይ ማስመዝገቡ ነው፡፡ ይህ ከ15 ሚሊዮን የማይበልጥ ተናጋሪ ያለው ቋንቋ ከ62 ሚሊዮን የበለጠ ተናጋሪ ያለው አማርኛ  ጋር ያላቸው ልዩነት አይመጣጠንም፡፡ የካታላን ቋንቋ በስሩ ከ402 ሺ የበለጡ ጽሁፎችን ሲይዝ የአማርኛ ቋንቋ ግን 12 ሺ ያህል ጽሀፎችን ይዟል፡፡ ይህም 12ሺ ጽሁፍ ከ6 ባልበለጡ አስተዳዳሪዎች ኤዲት የተደረገ ነው፡፡ ይህ ከፍተኛ የመጠን ልዩነት ከየት የመጣ ነው? የካታላን ቋንቋ በሶስት ሃገሮች ከ15 ሚሊዮን ባነሰ ህዝብ ይነገር እንጂ ከሌሎች በተለይም ከስፓኒሽ ተናጋሪዎች ጋር ያላቸው ግጭት ለዚህ ልዩነት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ሳያደርግ አይቀርም፡፡ በስፔን ስር የሚገኙ ካታላን ተናጋሪዎች የሚገኙበት ክልላዊ መንግስት ለቋንቋው ማደግ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ሳያደርግ አይቀርም ይባላል፡፡ እንደሚባለው ክልላዊ መንግስት ለዚሁ ብቻ ሲባል ቋንቋው በኢንተርኔት ላይ ያለውን አሻራ የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች ላይ አትኩሮ የሚሰራ ተቋም አለው፡፡ በዚህም ምክንያት አሪፍ የተባሉ ስነጽሁፎች፣ ቲያትሮችና መጻህፍት ወደ ካታላን ቋንቋ ተተርጉመዋል፡፡ ካታላን ቋንቋ ለካታላን ህዝቦች የማንነታቸው አንድ መሰረት ነው፡፡ ለዚህም ነው በመንግስት ደረጃ ቋንቋውን ለማሳደግ የሚደክሙት፡፡ አማርኛ ወይንም ሌላውም የሃገራችንን ቋንቋ በሌላ ወገን እንደምሳሌ ዊኪፒዲያን ወሰድነው እንጂ  በኢንተርኔት ላይ ያለው አሻራ ኢምንት ነው፡፡ በመሆኑም የሚከተሉትን መፍትሄዎች ብንጠቀም ችግሩን ልንቀርፍ እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡                
1.      ሃላፊነቱ ያለባቸው የትምህርት ተቋማት፣ የባህል ሚኒስተር፣ የማስታወቂያ፣ የመገናኛና ኢንፎርሜሽ ሚኒስትር መስሪያቤቶች እንዲሁም ሌሎች የመንግስት  አካላት የተሰጣቸውን ሃላፊነቶች በይበልጥ እንዲወጡት...ካልተሰጣቸውም በአዋጅ ስራቸውን በማሻሻል እንዲያከናውኑት ማድረግ፡፡
2.     ሃገር የምታድገው በንግድና ኢንደስትሪ ብቻ አይደለምና ዜጎች ለሃገራቸው ባህልና ቋንቋ ቅድሚያ እንዲሰጡ ማስተማር
3.     በተለይ ኢንተርኔትን በተመለከተ ግለሰቦች ከመንግስታት የበለጠ ጉልበት አላቸውና ተማርን ነቃን የምንል ነገ የምትተርፍ ሃገር እንድትኖረን መጣር ይገባናል፡፡
     
      ለምሳሌ ጥቂት ማድረግ የምንችላቸው ጥረቶች ይኖራሉ፡፡ የስፓኒሽ ዊኪፒዲያ ከዋናው ዊኪፒዲያ ጋር በነበረው ጠብ ምክንያት ተለያይቶ ወጥቶ የስፓኒሽ ሃገራዊ እውቀቶችና ባህል ላይ የሚያተኩር የራሱን Enciclopedia Libre Universal en Español የተሰኘ የእውቀት ባህር ከፍቷል፡፡ ስለዚህ እኛም ወይ በዋናው ዊኪፒዲያ ስር ወይንም ይበልጥ በተደራጀና ቁጥጥር ባለው  ሁኔታ የራሳችንን ኢንሳይክሎፒዲያ መፍጠር እንችላለን፡፡ በመጻህፍት ያከማቸነውን እውቀት መቼም ዘመኑ ነውና ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ይገባናል፡፡ይህንን ለማሳካትም የተጀመሩ ጥረቶችን ለመደገፍ ሊቋቋም የታሰበ ፕጀሮጀክት አለ፡፡ የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ሃሳብ የወል ጥረት ውጤት የነበረው wikipedia.org ላይ በተጀመረው የአማርኛ ፕሮጀክት ስር በተደራጀ ሁኔታ በበጎ ፍቃደኞች የሚተረጎሙና የሚጻፉ ወጥ ጽሁፎችን ማዘጋጀት ነበር፡፡ ይህንንም ለማሳካት  ኢትዮጵያውያን በወደዱትና በሚያውቁት የእውቀት መስክ የተመረጡ ጽሁፎችን በማዘጋጀት በተለይ የሃገር ውስጥ ተማሪዎችን ጠቅላይ እውቀት በእናት ቋንቋቸው እንዲያገኙ ማድረግ ነበር፡፡ ይሁንና በተለይ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ዊኪፒዲያ ድረገጽ እያስተናገደ ካለው ትችት አንጻር ከዛ የሚገኙ ጽሁፎችን በሙሉ መጠቀም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለማንኛውም አንድን ድረገጽ ከፍቶ ማስተዳደር ያህል ቀላል ሆነው ይህ ፕሮጀክት አሁንም ከመንግስት ከመንግስታዊ ካልሆኑና ከግለሰቦች በተወጣጣ ቡድን እየተመራ ታሪክንና ሳይንስን፣ ጥበብንና መረጃን በሃገር ቋንቋ ለሃገር አዳጊ ልጆች ማቅረብ እንችላለን፡፡ ምናልባት በዚህ ሃሳብ ጉዳይ ላይ የተለየ፣ ተጨማሪ ወይንም መሳተፍ የሚፈልግ በኢሜል አድራሻዬ feruzj30@gmail.com በኩል ሊያገኘኝ ይችላል፡፡ ከአባቶቻችን የተቀበልነውን ቋንቋ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ማሳደግና ለትውልድ ማስተላለፍ ግዴታችን ነው፡፡ ይብቃኝ ሃሳቦቻችሁንና ጥያቄዎቻችሁን እጠብቃለሁ፡፡ አመሰግናለሁ....ኢትዮጵያችን ለዘላለም ትኑር!


ጸሃፊው ፌሩዝ ጀማል በሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 ሬዲዮ በ IT, ድምጽ ላይብረሪና ፕሮግራም ትራፊክ ሃላፊነት ይሰራሉ፡፡ ጸሃፊውን ለማግኘት በፌስ ቡክ ገጻቸው https://www.facebook.com/feraj?ref=tn_tnmn  በኢሜላቸው feruzj30@gmail.com መጠቀም ይቻላል፡፡


No comments:

Post a Comment