Total Pageviews

Saturday, April 13, 2013

እንከን አይወጣለትም!


የማወራችሁ ስለ 11 አመት ታዳጊ ነው፡፡ የኔ ግምት 8 ወይም 9 ነው፡፡ እሱ 11 ነኝ ስላለኝ ተጠቀምኩት እንጂ፡፡

    ከፒያሳ ወደ አዲሱ ገበያ መስመር ላይ በተለያዩ ታክሲዎች ላይ ወያላ ሆኖ ይሠራል፡፡
የመጀመሪያ ቀን ፒያሳ "አዲሱ ገበያ ሰሜን ሆቴል የሞላ የሞላ 2 ሠው" እያለ ደጋግሞ ሲጠራ ይህ ልጅ ወያላ ነው ለማለት ተቸግሬ ነበር፡፡ ታክሲ ውስጥ ያለው ሁሉ በአግራሞት እያየው ከንፈር ይመጣል፡፡

     ታዳጊው ከእድሜው በታች በጣም ቀጫጫ ነው፡፡ ጉዞ ጀምረን ገንዘብ ሲሰብሰብ እጁ ዝርዝር ሳንቲሞች ለመያዝ ተቸግሮ አሁንም አሁንም ኪስ ወደ ተሞላች ሱሪው እጁን ይሠዳል፡፡ ድንገት ስራውን ዘንግቶ በታክሲ ካሉት ህፃናት ጋር ይጫወታል፡፡ ደግሞ መለስ ይላል፡፡ ታክሲ ውስጥ ካሉት አብዛኛዎቹ ያላቸውን መልስ ሳይቀበሉ ትተው ወረዱ፡፡ከዛ በኋላ ከአማኑኤል ጋር ደጋግመን ተገናኝተናል፡፡

እንዲህ ያለውን አቅምና እድሜን ያላገናዘበ የጉልበት ስራ ለኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ5 እስከ 14 የሆኑ 60 በመቶ ህፃናት ይጋሩታል፡፡ያውም በከፋ መንገድ፡፡  

     ይህ በአለም የህፃናት ጉልበት ከሚበዘበዝባቸው 10 ፊት አውራሪ የአለም አገሮች ኢትዮጵያን አንዷ  አድርጓታል፡፡
በሒልተን ሆቴል በተዘጋጀ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን የተመለከተ ስብሠባ ላይ እንድሳተፍ ተጠራሁ፡፡ እንደ ጋዜጠኛ ብዙ ልሠማ ሄድኩ…ግን ብዙ እንድናወራ የሚጠበቅበት ሆኖ አገኘሁት፡፡ ‹‹ቶክሾው›› መሆኑ ነው፡፡
ፕሮግራሙን የሚመራው ጋዜጠኛ ... (አሁን ስም ምን ያደርጋል?) ይህ የሚያክል ትልቅ ሀሳብ በ3 ደቂቃ እንዲገባደድ የሚናገሩትን ጋዜጠኞችና ‹ባለድርሻ አካላት
(የሚመለከታቸው እንደማለት ነው)፤ አፍ አፋቸውን ይላል፡፡ የሚጀመር እንጂ የሚያልቅ ሀሳብ ጠፍቷል፡፡  ባለሙያዎቹ እንዲህ አይነት ጥፋተኞችን ለመቅጣት በቂ ኧረ እንደውም ከዛ በላይ ህግ ወጥቷል ግን ተፈፃሚ አይደለም ይላሉ፡፡ አብዛኛው ሰው ግን የግንዛቤ እጥረት›› የምትለው ሃሳብ ላይ የሙጠኝ ብሎ ይዘምራታል፡፡

 ወይ ጣጣ
     ‹‹የግንዛቤ እጥረት የግንዛቤ እጥረት "የግንዛቤ እጥረት"  ይላል፡፡ እንዴት እጅ እጅ ይላል ይህ ቃል? በግንዛቤ እጥረት የተናገሩት ይሆናል ብልን እንለፈው፡፡ እኛ ሀገር ሁሉም ነገር በግንዛቤ እጥረት የመጣ ነው፡፡

እድሜያቸው ከ15 አመት በታች የሆኑ ልጆችን ከባባድ ስራ ማሰማራት ያስቀጣል፡፡ በህግ ተደንጓል! አንቀጽ ወጥቶለታል! ወንጀል ነው!
በየቤታችን አንድ ለልጅ አቃፊ፣ አንድ እግር አጣቢ፣ እያልን ህፃናትን ከገጠር ስንመለምል ወይም ሽሮሜዳን ያጥለቀለቁትን የሚታዩና የማይታዮ ህፃናትን ጉልበት ስንበዘብዝ እንታያለን፡፡ ድርጊቱን የሚፈፅሙት እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ወጪ ለመቆጠብ፤ የፍላጐት ያህል ጉልበት ለመበዝበዝ፤ ትርፍ ለማጋበስ ይህ ሁሉ ጥቅም ነው፡፡
ሲጋራ ማጨስ እንደሚጐዳ አጫሹ ያወቀዋል ግን ያደርገዋል፡፡ ተያያዥ የሆነ  አካባቢያዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊኖርውም፣ ይህ ሰው የሚጐዳው ራሱን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህን አጫሽ የግንዛቤ እጥረት አለበት ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ በሌሎች ህይወትና ሬሳ ላይ ቤቱን የሚያቆምና ህንፃ የሚሠራን እንዴት ግንዛቤ  አጥሮት ነው ተብሎ "እንከን አይወጣለትም" የተባለ ህግ ሳይፈፀም ይቀራል?
አታምርሪ እንደምትሉኝ አውቃለሁ፡፡ ግን ልቀጥል ትንሽ እድል ስጡኝ፡፡
ሌላው ተደጋግሞ ሲነሳ የነበረው ምን መሰላችሁ? "ህብረተሰቡን ለወንጀል ተባባሪ ሆነ ጥፋተኛን አያጋልጥም" የሚል ወቀሳ ነው››
ሀገር ያወቀው ፀሃይ የሞቀው የአደባባይ ጉዳይ ከህዝቤ ካልሠማሁ አላምንም የሚል ከአይኑ ይልቅ ህዝቡን የሚያምን ብቸኛ መንግስት የኛ ሃገሩ ይመስለኛል፡፡

ስለ ኢትዮጵያ ማውራት ይቅር .... አዲስ አበባ ላይ ሰብሰብ እንበል፡፡ ስለሽሮ ሜዳዎቹ ህፃናትም አናንሳ .... በየቤቱ ተጫውተው ሳይጠግቡ አጫዋች የሆኑ፣ ቤታችንን ቀጥ አድርገው የሚያስተዳድሩ፣ የንዴትና ብስጭታችን ማራገፊያ የሆኑ ህፃናት ጉዳይንም ተዉት፡፡  
..... የወያላዎቹንም ህፃናት ጉዳይ አታንሱት፡፡ ሁሉንም እርሱት፡፡

ጋዜጠኝነት እግር ጥሎ የሚያደርሠን ቦታ ብዙ ነው፡፡
ይህ የመስሪያ ቤቶች የሻይ ክበብን ይጨምራል፡፡ በብዙዎቹ ደርሻለሁ፡፡ የሚያስተናግዷችሁ፣ ከለሊት ጀምሮ የምግብ እቃ፣ ወለልና ጠረጴዛ ሲያፀዱ የሚውሉ እነዚሁ እምቦቃቅላ ህፃናት መሆናችሁን ልብ ብላችኋል? ... እውነት እስኪ ስራዬ ብላችሁ ተመልከቱት፡፡
ስለነዚህ ህፃናት አዝነው ሳያበቁ፣ ያሉበት ክበብ መዝናኛ ቤቶች የህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚንስቴር ወይም ቢሮ መሆኑን ቢያውቁ ምን ይሠማዎታል፡፡
ማታ በቴሌቭዥንዎ የዜና ሰዓት ‹‹የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ይበቃ›› የሚል ቲሸርትና ኮፊያ አድርጐ ንግግር ሲያደርግ ያያችሁት ሰው ‹‹አንተ ማነህ..... እያለ ትዕዛዙን ሲያዥጐድጐድ ይደመጣል፡፡

     በርግጥ እነዚህን ህፃናት አትወይሉ፣ አታስተናግዱ፣ አትጠቡ፣ አታፅዱ ማለት አትበሉም ማለት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ይህ ህይወት ወደው ሳይሆን ኑሮን ለማሸነፍ ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ ጥርሱን ያገጠጠውን ድህነት ለማምለጥ የገቡበት ነው፡፡

     አማኑኤል በቋሚነት የሚኖርበት ታክሲ ሳይኖረው በአጋጣሚ ከወያላቸው ተጋጭተው ወይም በሌላም ምክንያት ያለ ገንዘብ ያዥ የሚወጡ ተሸከርካሪዎች ላይ እየተገለባበጠ እንደሚሠራ ያወኩት  በቅርብ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ከብዙ መሰሎቹ ተጋፍቶ የሚያገኘው ሎተሪ ነው፡፡ አብዛኛው ባለስልጣን ለስርዓቱ ስም ሲል ችግሩን አጐልቶ ማውራት ይፈራል፡፡ ለውጡ ላይ ከስር ከስር እየሠራ ነው እንዳይባል የሚመለከተው በማይመለከተው ጉዳይ ተጠምዷል፡፡

     የስርዓቱ እድሜን የሚያረዝም የሚመስል አንድ ጉዳይ ይዞ ችክ ምንችክ ከማለት ለህዝቡ ለውጥ የሚመጣው ላይ መረባረቡ ይሻላል፡፡ እንደኔ ለውጡ እድሜ ማምጣቱ አይቀርምና፡፡
እናንተ ምን ታስባላችሁ?  




ጋዜጠኛ ሃኒ ሰለሞን ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቀዋል፡፡ አሁን በሸገር ኤፍ.ኤም ሬዲዮ በጋዜጠኝነት በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሃሳብና አስተያየት ካለዎት በኢሜላቸው honeysolomon123@yahoo.com በፌስቡክ ገጻቸው https://www.facebook.com/honey.solomon.3 ሊያገኟቸው ይችላሉ፡፡

5 comments:

  1. Hony,You said that very well, and I agree. Indeed, there are so many reasons to say about child labor, but the point is, nowadays, it is one of the most fundamental problems facing as a society. The future depends on how we solve this problem. It has never been encountered before. Who could have thought... a child and a slave? A slave to his own parents & his own society, who love him, who sacrifice themselves for the child? It would have looked ridiculous, utter nonsense! Laws do not persuade just because they threaten. Let us consider the reason of the case. For nothing is law that is not reason.

    ReplyDelete
  2. This comment has been removed by the author.

    ReplyDelete
  3. hany. endesmsh ahny nesh batekalay sheger. ewodachhalewu lezelalem nuru

    ReplyDelete
  4. ምን እንባ ነበረሽ ከራሔል ያነሰ፤
    እንባ አይመስልም እንባ ጊዜውካልደረሰ።
    .........
    ~የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ

    ReplyDelete