ልማትን አጥብቆ የሚወደው ኢ-ቲቪያችን የቦሌን መንገድ አስመልክቶ
አንድ የቢዝነስ ወሬ አቀረበ፡፡ ከመስቀል አደባባይ አውሮፕላን ማረፊያ (ቻይና አደባባይ መሠለኝ) ያለው መንገድ ስራ አልቆ ሙሉ
በሙሉ ስራ ላይ ውሏል አለ፡፡ እናም በመንገዱ ስራ ምክንያት ስራቸው ቀዝቅዞባቸው የነበሩት የንግድ ቤቶች አሁን ገበያው ድርላቶቸዋል
ብሎም ጨመረ፡፡ አንዳንድ ገበያችን ከ 70 በመቶ ወደ 85 በመቶ ጨምሯል የሚሉ ጥናት ሳይሰሩ በመቶኛ መነጋገር የሚቀናቸውን ነጋዴዎችም
አስተያየታቸውን ሰጡ ፡፡ አይ ጥሩ ነው እንኳንም ገበያችሁ ደራ ብለናችኋል፡፡ እነዛ የመንገዱ ስራ በተባለው ጊዜ ባያልቅ ቤተሰቤን
ምን እመግባለሁ ብለው የሰጉ ነጋዴዎች ግን ንግዳቸውን ወደ ሌላ ሰፈር ቸኩለው አዛወሩ፡፡ ይሄው ዛሬ ሁለት ጉድጓድ ያላት አይጥ
እንደሚባለው ሌላ ሰፈር መተዳደሪያ ሱቅ የነበራቸው እና አንዳንድ
ተስፋ በቀላሉ የማይቆርጡ ነጋዴዎች ጥርሳቸውን ነክሰው ሰንብተው በዛሬው
የደራ ገበያ ፈገግ ፈገግ ለማለት በቁ፡፡ ከዚህ ወጣ ያሉት የቦሌን መንገድ በእግርና በታክሲ የሚያቋርጡት መኪና የሌላቸው ዜጎች
ግን ‹ስራው ተጠናቀቀ› የተባለው የቦሌ መንገድ ‹መቼ ተጠናቀቀና?› እያሉ ነው፡፡
ሚዲያዎች ማንን መሠረት አድርገው እንደሆነ እንጃ መንገዱ ተጠናቋል ብለው
ይዘግቡ ከጀመሩ ሰነበቱ፡፡ ባለስልጣናትም ከሳምንታት በፊት በመንገዱ አካፋይ ላይ ለምለም ቅጠል ሻጥ ሻጥ ተደርጎላቸው ስራችንን
ጨረስን መኪናም አስተላለፍን ብለው መጥተው መረቁት፡፡ እርግጥ ቅጠሎቹ አሁን ደርቀዋል፡፡ የአስፋልት ጥቁረት ምን መምሰል እንዳለበት
የሚከራከሩ ባለመኪኖች ደግሞ ‹መንገዱ አላለቀም፡፡ ምክንያቱም ይሄ ጭቃ መሰሉ ነገር ጠፍቶ ድብን ያለ ጥቁር መሆን ስለሚገባው ገና
አንድ ዙር አስፋልት ማልበስ እና ማስዋብ ይቀረዋል፡፡› እያሉ ነው፡፡ እነዚህ ባለመኪና የመንገዱ ተጠቃሚዎች በፊት በፊት ‹የቦሌ
መንገድ የትራፊክ መጨናነቁ ገደለን መንገዱ ሰፋ ቢል ጥሩ ነበር፡፡› በሚል አብዝተው ሲማረሩ የኖሩና አሁን ፀሎታቸው ተሰምቶ የመንገዱ
ስፋት የሚሆኑበት ጨንቋቸው በከፍተኛ ፍጥነት እየበረሩበት ያሉ ናቸው፡፡ ዛሬ ጠዋት አንዲት እናት ዕድሜአቸው በማይፈቅደው ሩጫ ነፍሴ
አውጪኝ ብለው አስፋልት ከተሻገሩ በኋላ ቁና ቁና እየተነፈሱ እንዲህ አሉ ‹አሁንማ መንገዱም ሰፋላቸው!›፡፡ ባለመኪኖቹ በመንገድ
ግንባታው ወቅት መንገድ ቀይረው፣ በመንገዱ መጣበብና መጨናነቅ ለረዥም ደቂቃዎች መኪናቸው ውስጥ ተቀምጠው ያሳልፉ የነበረበት ጊዜ
ላይ ለመሳለቅ ይመስላል አሁን በአጭር ደቂቃ የፈለጉት ቦታ የመድረሳቸውን ተዓምር እያደናነቁ እንደጉድ ይበራሉ፡፡ እያደናነቁም ግን
‹መንገዱማ የማስዋብ ስራ›ይቀረዋል ይላሉ፡፡
የቦሌን መንገድ በስራም ሆነ በመተላለፍ አጋጣሚ የሚያዘወትራት እግረኛ
በተመሳሳይ/በሚያስገርም ተቃርኖ ‹የቦሌ መንገድ አላለቀም!› ብሎ በድፍረት እየተናገረ ነው፡፡ ምክንያቱም የእግረኛ መረማመጃው ገና
ኮረት እንደተከመረበት ነው፡፡ ጉድጓድም ሞልቶታል፡፡ እግረኞች የእግረኛ መንገዱ ገና በስራ እና በቁፋሮ ላይ በመሆኑ ከፈጣን መኪኖች
ጋር ትከሻ ለትከሻ እየተጋፉ በመኪና መንገድ ላይ እየተጓዙ ነው፡፡ መሻገሪያ መራመጃ አጥቶ ሁለት ዓመት የተንገላታው እግረኛው ነው፡፡
ታክሲ የሚሳፈርበት እና የሚወርድበት ቦታ አልመች ብሎት ለልማቱ ሲባል ‹ቻለው› የተባለው እግረኛው ነው፡፡ አቧራ እና ጭቃ ተፈራርቆበት
ለዓይንና ለባክቴሪያ ህመም እና የህክምና ወጪ የተዳረገው እግረኛው ነው፡፡ 3 ብር ከ70 ይከፍልበት ለነበረው መንገድ 8 ብር እየከፈለ
የሄደው እግረኛው ነው፡፡ ለእግረኛው መንገዱ የሚጠናቀቀው ስቃዩ ሲጠናቀቅ ነው፡፡
አዲሱ የቦሌ መንገድ አምሮበታል፡፡ መኪና የሌለው ደሀ (እግረኛ) አልይ ያለ ይመስላል፡፡ በየመሀሉ ለእግረኛ የሚሆን መቋረጫ እንዲኖር አልፈቀደም፡፡
ታክሲዎችም እዛም እዛም እየቆሙ እንዲጭኑና እንዲያራግፉ አይወድም፡፡ ስለዚህ እግረኛ ስሙም ከነመጠሪያ እግረኛ ነውና በእግሩ እንዲሄድ
ተፈርዶበታል፡፡ ለምሳሌ ከፒያሳ ደንበል ህንፃ ድረስ በታክሲ መምጣት የሚፈልግ ሰው ቀደም አድርጎ ፍላሚንጎ ጋር ወርዶ በእግሩ እንዲሄድ
ይጠየቃል፡፡ ባለታክሲዎቹ መንገዱ በሙሉ ‹ክልክል በክልክል› ሆነብን ብለው ያማርራሉ፡፡ ማውረድ ክልክል ነው፡፡ ተሳፋሪውም ታሪፉ
እንኳን ቢቀነስልን ብለው ያሳቅላሉ፡፡ አንድ ወቅት ላይ የህዝብ ማመላለሻ ዋጋ ታሪፍ በመንግስት አባባል ‹ሲሻሻል› በህዝቡ አቀባበል
ደግሞ ‹ሲጨምር› ይመለከተኛል ያለው የመንግስት አካል ህዝቡ በኪሎሜትር መክፈል ያለበትን ዋጋ በጋዜጣ አትሞት ነበር፡፡ ለአብነት
ያህል በጋዜጣው ስሌት መሠረት ከፒያሳ ደንበል ሸዋ ዳቦ የሚወስደው የታክሲ ዋጋ 2 ብር ከ70 ሳንቲም ነው ብሎ አወጀ፡፡ ጋዜጣውን
እማኝ አድርገው መክፈል ያለብን 2፤70 እንጂ 3፡70 አይደለም ብለው የተከራከሩ ተሳፋሪዎች ከታክሲ ሾፌሮች ግልምጫ ከረዳቶቸ ደግሞ
እርግጫ (ቀረሽ) ምላሽ ሲደርስባቸው ብሶታቸውን ለሚመለከተው አምላክ ሰጥተውት ዝም አሉ፡፡ የቦሌው አዲሱ መንገድ ደሀውን ከሳንቲሙም፣ከጉልበቱም
ከጊዜውም፣ በጥቅሉም ከልማቱም ያስተረፈለት የለም፡፡ ታዲያ መንገዱ ለደሀው እግረኛ ምኑ ነው? ለባለመኪና ፍጥነት ጨምሯል ለእግረኛው
ስቃይ ጨምሯል፡፡ እንግልትም ምቾትም እንዴት ላለው ይጨመርለታል?
አንዳንድ ሀገራት ለህዝባቸውም ርካሽ የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፓርት ማቅረብ ሲታክታቸው ሰፋፊ መንገዶችን ይሠሩና ህዝባቸው መኪና እንዲገዛ ያበረታታሉ፡፡ በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ መንገዶች
ለእግረኞች ሳይሆን ለባለመኪኖች እንዲመቹ ተደርገው እየሰፉ ነው፡፡ እግረኛው በእግሩ እና በታክሲ መሄድ አላዋጣው እንዲለውና የራሱን
መኪና እንዲገዛ ከሆነ እሰየው፡፡ ሆኖም መኪና የገዙ ፣ለመግዛት ያሰቡ በአጠቃላይ የመግዛት አቅሙ ያላቸው ሰዎች መኪና ቀረጥ መቶ
ሀምሳ እጥፍ መሆኑ የሚቀመስ አላደረገው እያሉ እያማረሩ ነው፡፡በዛ ላይ ገንዘቡስ ከየት ይመጣል? በሌላ በኩል ጠባብ መንገድና ከተማ
እንዲሁም በርካታ ህዝብ ያላቸው ሀገሮች የመኪና ዋጋን ሳይሆን የመኪና ማቆሚያ ስፍራ በማሳጣትና ኪራዩንም በማስወደድ መኪና ለምኔ
ብሎ እንዲተውና በተለይም በከተማ ባቡር እንዲጠቀም ያደርጉታል፡፡ አዲስ አበባ የከተማ የባቡር መንገድ እየተዘረጋ መሆኑ ህዝቡ መኪናም
ባይኖረው የትራንስፓርት ፍላጎቱ እንዲሟላለት ይመስላል፡፡ የሚመስለንን
ትተን እውነቱን እንጠይቅ፡፡ መንግስት ህዝቡ መኪና እንዲኖረው ፈልጓል ወይስ አልፈለገም? መንገድን ለማን ነው የሚሰራው? ለሞላው
ለተደላደለው? ወይስ ላጣው ለነጣው? የቦሌው አዲሱ መንገድ በሁሉም የኢኮኖሚ ደረጃ ያሉትን ዜጎች እኩል ለማገልገል ታስቦ እንዳልተሰራ
እያሳበቀ ነው፡፡ ለደሀው ተብሎ የለማው መንገድ የቱ ነው? ልማት ማለትስ ምን ማለት ነው?
ጸሃፌ ተውኔት መዓዛ ወርቁን በሸገር የአልጋ በአልጋ ተከታታይ ድራማና በህይወት መሰናዶ ድራማ ደራሲነታቸው እናስታውሳቸዋለን፡፡ አሁን እየታየ የሚገኝ ዝነኞቹ የተሰኘ ቴአትርም አላቸው፡፡ አስተያየት ካላችሁ በፌስቡክ አድራሻቸው በኩል በhttps://www.facebook.com/meaza.worku.39 ሊያገኙዋቸው ይችላሉ፡፡
ጸሃፌ ተውኔት መዓዛ ወርቁን በሸገር የአልጋ በአልጋ ተከታታይ ድራማና በህይወት መሰናዶ ድራማ ደራሲነታቸው እናስታውሳቸዋለን፡፡ አሁን እየታየ የሚገኝ ዝነኞቹ የተሰኘ ቴአትርም አላቸው፡፡ አስተያየት ካላችሁ በፌስቡክ አድራሻቸው በኩል በhttps://www.facebook.com/meaza.worku.39 ሊያገኙዋቸው ይችላሉ፡፡
meaza !!!Really you are good observant for the good of the people .
ReplyDeleteShame to ETV and some fake journalists who are always exaggerating things which is not yet done.
Thank you.
I feel your frustration Meazi! I have faced the same problem when walking on Bole road. But it hasn't been all roses for the drivers as well. For starters one can not stop at any part of the Bole road even for few minutes. (Many business owners are complaining about that by the way)On top of that the distance you have to take to make a U turn on the new Bole road wastes time as well as the very expensive Benzine. So I say Bole Road looks beautiful from a distance but has lots and lots of problems for both drivers and pedestrians.
ReplyDeleteAre you serious? Are complaining about this road. You should be mad. Coz kelimat gar ena ke ediget gar teyayizo mimetutin chigiroch hizbu betigist endiyalf madreg new. Chigir binoris birk new? Kes tebilo yikerefal. Mindinew yihe hulu negetiv diskur??? Man yitekemal kezih negetive tsuf? Bayseras noro? Please you so called "journalist" try to write something positive.
ReplyDelete