ከአመታት በፊት በአንድ አጋጣሚ በአውሮጳ በአንዱ
ከተማ ለጥቂት ቀናት ያገኘነው ወጣት እጅግ ለጋስ በሆነው በአገራችን ልጆች መስተንግዶ ካስተናገደን በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮች
አውጥቶ ለአባቴ ስጡልኝ አለን፡፡ የወጣቱን ልጅ ኑሮና እጅግ የበረታ የሥራ ድካም በሁለት ቀን ዕድሜ ጥሩ አድርገን አይተነው ነበርና
ምነው አይበዛም? አንተ እዚህ አልተመቸህ? አልነው በማያገባን ገብተን፡፡ አባቴ የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ውጤት ጥሩ ስላልመጣልኝ ለዓመታት
እቤት ውስጥ እውል ነበርና፤ እግቢያችን ውስጥ ያለውን የኰክ ዛፍ እያሳየ “አንተና ይሄ የኮክ ዛፍ አንድ ናችሁ አታፈሩም”! ይለኝ
ስለነበር እዚህ መጥቼ ያጠራቀምኩትን የመጀመሪያ ገንዘብ ማፍራቴን እንዲያይ መላኬ ነው፡፡ ማለቱን መቼም አልረሣውም ፡፡
በየአገሩ የተበተኑት ኢትዮጵያውያን ከያሉበት
አገር ወደ አገር ቤት ገንዘብ ሲልኩ ስሰማም ሆነ ሳይ የዚያ የወጣት አነጋገር በሃሳቤ ይመጣል፡፡ በየጊዜው የሞራል ስብራት ያደረስንባቸው
ልጆቻችን የልጅነት ወዛቸውንና ጉልበታቸውን እያፈሰሱ ያላቸውን ጥሪት እየላኩ የሞራል ስብራታቸውን እየጠገኑ፣ ቁጭታቸውን እየተወጡ
ይሆን?
የአለም ባንክ የቅርብ ጊዜ መረጃ 215 ሚሊዮን ሰዎች ከትውልድ አገራቸው ውጪ ይኖራሉ ይላል፡፡
ከእነዚህ ሰዎች ወደየትውልድ አገራቸው የሚላከው ገንዘብ ከተለያዩ አገሮች በልማት ስም ከሚሰጠው ዕርዳታ በሦስት እጅ ይበልጣልም
ይላል፡፡ ይሄም በገንዘብ ሲሰላ በ2011 ብቻ 372 ቢሊዮን ዶላር በ2012 530 ቢሊዮን እንደደረሰ የአለም ባንክ ሪፖርት ያመለክታል፡፡
ቁጥሩም በየዓመቱ እየጨመረ እንደሚሄድ ያሳያል፡፡ ይሄ እንግዲህ እንደ አለም ባንክ መረጃ፤ ፀሐይ
ሞቆት አገር አውቆት በባንክ በኩል የሚካሄደውን የገንዘብ ዝውውር እንጂ የአድርሱልኙንና ሌላ ሌላውን አይጨምርም፡፡
ይሄን መረጃ መነሻ አድርገው የኤኮኖሚ ባለሙያዎች
ከበለፀጉ አገሮች ከሚላከው የገንዘብ እርዳታ ይልቅ በየአገሩ ኗሪ ከሆኑ ስደተኞች የሚላከው ገንዘብ ከዕርዳታው ድጐማ በሦስት እጥፍ
የሚበልጥ ከሆነ የትኛው አማራጭ ይበጃል? እያሉ ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የሚበጀው በብዙ የእርዳታ ውለታ የማይታሠረው
የአገር ልጆች በፈቃዳቸው የሚልኩት ገንዘብ ይመስለኛል፡፡
እነዚህ ኤኮኖሚስቶች በግልጽ የማይናገሩት፣ ግን
“ስደተኞች ወደ አገራቸው የሚልኩት ቢሊዮኖች ዶላሮች ሳቢያ የለጋሽ አገሮች እርዳታ ጥላ ጥሎበታል” በሚለው ዜና ሥር ሥር የሚሄድ
አንድ ስጋት ያለ ይመስላል፡፡ ምናልባት ስጋቱ እነዚህ እርዳታ ጠባቂ አገሮች
ሁለት ጥቅም ይዞ የሚላክላቸውን እርዳታችንን ከቁብ መቁጠር ያቆማሉ የሚል ነው እንበል? ማን አላችሁ? ተብሎ ቢጠየቅ እገሌ በማይባልበት
የድፍረት አነጋገርም “የኛም በፖለቲካ ወዘተ ወዘተ ተጽእኖ የማሳደር አቅማችን እየቀነሰ ይመጣል” የሚል ይመስላል እንበል፡፡ እንግዲህ
ከተወላጆች ወደ አገር ቤት የሚላከው ገንዘብ እያደገ ከሄደ ብዙ የለጋሾችን እጅ ጠባቂ አገሮች ጠባያቸው መቀየሩ አይቀሬ ነው፡፡
እንዲያውም አንዳንድ አገሮች ርዳታውን ከአገሬ ልጆች አገኘዋለሁ እያሉ እያስፈራሩ መሆኑ ይነገራል፡፡
በእርዳታም ይሁን በውጭ ኢንቨስትመንት ተደምሮ
ከሚመጣው ገንዘብ ይልቅ በአገር ልጆች ወደ አገር ቤት የሚላከው ገንዘብ ከሚበልጥባቸው አገሮች መካከል ባንግላዴሽ፣ ሜክሲኮንና ሴኔጋልን
መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተለይ ጠዋት ለቤተሰብ የተላከው ገንዘብ ምሽት
ላይ በኢንተርኔትና በስካይፕ ቤተሰብ ምን እንዳደረገበት በአይን ሲታይ ላኪውን ይበልጥ ማስደሰቱና ማርካቱ ላኪዎችን ማትጋቱ በየዓመቱ
የገንዘቡን መጠን አሳድጐታል ይላሉ በዋሽንግተን የ Center for Global Development አጥኚ ማይክል ክሌመንስ፡፡
የማህበረሰብ ተሟጋች ተቋማት ደግሞ ይሄ ገንዘብ
በሥራ ሰበብ ብዙ እንግልትና ጉዳት የሚደርስባቸውን በየአገሩ የሚሰደዱ ዜጐችን መከራ ሊያስረሣ አይገባም፡፡ የኤኮኖሚ ስደተኞች መብት
መከበር ይኖርበታል ይላሉ፡፡ ለመቆጣጠር አለም አቀፍ ሕግ ወጥቷል፡፡
ብዙ መንግሥታት ግን አልፈረሙትም ከእነዚህ መካከልም አሜሪካና የአውሮፓ አገሮች እንዲሁም የገልፍ አገሮች ይገኙበታል፡፡
በእኛም “አገር ሣሩን አየህና” እየሆነ ብዙ
ወጣቶች በየድንበር ኬላውና በየአገሩ የሚደርስባቸውን እንግልት በየቀኑ እንሠማዋለን፡፡ ይሄን የስደተኛ ሠራተኞችን ችግር በየአገሩ የተሠራጩትን የአገር ልጆች ገንዘባቸውን መውደድ ብቻ ሳይሆን ለደህንነታቸውም
መከራከር ይገባል፡፡ ያገራችን ተረት ምን ነበር?
የአገር ልጅ
የማር እጅ?
እናንተስ ምን ትላላችሁ?
ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የቆዩ የሬዲዮ ጋዜጠኛ ናቸው፡፡ ላለፉት አስራ ምናምን አመታት በየጨዋታ እንግዳ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ለጋዜጠኛ መዓዛ የምንለው አለን የምትሉ meaza.birru@shegerfm.com ይጻፉ፡፡ ወይንም በዚሁ ብሎግ ላይ አስተያየታችሁን ማስፈር ትችላላችሁ!
ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የቆዩ የሬዲዮ ጋዜጠኛ ናቸው፡፡ ላለፉት አስራ ምናምን አመታት በየጨዋታ እንግዳ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ለጋዜጠኛ መዓዛ የምንለው አለን የምትሉ meaza.birru@shegerfm.com ይጻፉ፡፡ ወይንም በዚሁ ብሎግ ላይ አስተያየታችሁን ማስፈር ትችላላችሁ!
ለዛ ያለው ወግ ማውጋቱን ተክነሽበታል…. የመገናኛ ብዙሀኖቻችን ‘ያለበት ሁኔታ ነው ያለው’ ን… በመሳሰሉ አሰልችና የተደጋገሙ ቃላት እንዲሁም ደግሞ በየቀኑ በማይቀየር ጭብጥና አቀራረብ በተሞሉበት ዘመን… እንዳንች ለዛ የለው ጥያቄ የሚጠይቅ፣ ወግ የሚወጋ… በጥናትና በተሞክሮ ላይ የተመሰረተ ስራ የሚሰራ ጋዜጠኛ ማግኘት መታደል ነው፡፡ እኛም ፀሎታችን እንደአንች አይነቶች እንዲበረክቱል ነው!
ReplyDeleteእኛም ፀሎታችን እንደአንች አይነቶች እንዲበረክቱል ነው!
DeleteThis comment has been removed by the author.
ReplyDeletelike
ReplyDeletemore love and respect Meazi, u r number one Ethiopian Journalist ../
ReplyDeleteHow best if we have more journalist like you. Really you are number one!!!!
ReplyDeleteበትክክል ሙያና ሙያተኛ የት ተገናኙ ቢባል አንቺንና ሙያሽ መጥቀሰ ሙሉ መልስ ነው ፡፡ ይህ አመዳደብ የተካሄደው ደግሞ ከላይ ከሰማይ መሆኑ ሁሉንም ያስማማል ብዬ አስባለሁ፡፡ ፈጣሪ ሁልጊዜ ካንች ጋር ይሁን!!
ReplyDeleteMeazi arife meleketa new Keep it up I appreciate Ur Radio program I wish Long Live for u and ur family
ReplyDelete