Total Pageviews

Wednesday, July 17, 2013

"ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ!"


በአንዲት ገጠር ከተማ የሚኖር አንድ ሰው ነበር አሉ፡፡  
ሰውየው መቃብር እየፈነቀለ ትኩስ አስክሬን አየጎተተ አውጥቶ መልሶ ይቀብራል፡፡ ግን ደግሞ የለበሱትን ልብስ ያጌጡበትን ጌጥ የደረቡትን ኩታ እያወጣ ይዘንጥበታል፡፡

ለዚህ ሰው የአንድ የአከባቢው ሰው ሞቶ እናም ተቀበረ ማለት ሀዘን ሳይሆን የደስታ ምንጭ ሆነ፡፡ ሰው ይሞታል ይቀበራል እሱም ሬሳውን አውጥቶ ልብሱንና ጌጡን ገፎ መልሶ ይቀብራል፡፡ ህዝብ ተማረረ፡፡ የፍትህ ያለ ቢልም መፍትሄ የሚሰጥ ጠፋ፡፡

መቸም ሰው ሆኖ ከአፈር የሚቀር የለምና ይህ ነውጠኛ ህዝብን ያስነባ ሰውም ተራው ደርሶ ሞተ፡፡ ፌሽታው በተራው የህዝቡ ሆነ፡፡ የአከባቢው ሰው ሆ ብሎ ደስታውን ለመግለፅ በነቂስ ወጣ…ስለቴ ሰመረ ያለ ፤ ወደ ፈጣሪው ያንጋጠጠም ብዙ ነበር፡፡ የሀዘን ሳይሆን የሰርግና ምላሽ ቀን መሰለ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ በሚያየው ነገር ያዘነና የተቆጨ አንድ ሰው  ነበር፡፡ እሱም የሟቹ ብቸኛ ወንድ ልጅ ነው፡፡
                        
                   ልጅ የአባቱን ስም በመልካም ሊያስጠራ ዛተ፡፡ ጭካኔው ግን ከአባቱ ከፋ፡፡

የተቀበረ አሰክሬን እያወጣ የፈለገውን ይወስዳል አስክሬኑን ሳይመልስ እንኳ ባለበት ጥሎ የሄዳል፡፡ ተቀበሩ የተባሉት ሰዎች አስክሬን አመሻሽ ላይ በጅብ እየተጎተተ የተለያየ  የሰውነት ክፍላቸውም ከነዋሪው ደጅ ላይ ሁሉ ይጣል ጀመረ፡፡ ሕዝብ እግዚኦ ፈጣሪ ምኑን ላከብን ሲል ኡኡታውን አለ፡፡ ኧረ አባቱ በምን ጣዕሙ እሱው ይሻል ነበር ቢያንስ እሬሳውን መልሶ አፈር ሳያለብስ አይሄድም ነበር ተባለ፡፡

                                ልጅ ዝቶም አልቀረ፡፡ አባቱን አስመሰገነ፡፡

ጡረታ የወጣሁ መምህር ነኝ ያሉ አንድ አባት ናቸው ያጫወቱኝ፡፡ አሳቸው የፈለጉትን ጉዳይ ለማስረዳት ተጠቀሙበት እኛ ደግሞ በታሪክ ፈረስ ጋልበን ዛሬ ላይ እንምጣ፡፡

ኢትዮጲያ በተለያየ ስርዓት እና  መንግስታት ስር አልፋ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ የስርዓትም ባይሆን በየግዜው የተለያዩ አዳዲስ የወንበር ለውጦች መደረጋቸውን ይሰማል ይታያልም፡፡ አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር አይተናል፡፡ ከሰሞኑ እንኳ ወሬው ሁሉ ሹመትና ሽረት ሆኗል…አዳዲስ ሚንስትሮች ፤ አማካሪዎች ፤ ከንቲባ ሌላም ሌላም፡፡

ስልጣኑን በሙስና ተዘፍቋል ተብሎ የተነጠቀ አለ፡፡ በአቅም ማነስ ፤ ከአንዱ ወደ አንዱ ለማገለባበጥ ታስቦ የተነሳ እና ቦታ የቀየረም አለ፡፡ ስራ ዘመኑን አጠናቆ የተሰናበተም አለ፡፡ ለኛ የማይታይ ምክንያትም ይኖር ይሆናል፡፡

እገሌ ሄዶ እገሌ ቢመጣም በአንድ ነገር እንግባባለን ፤ ህዝብ ሁሌም ከትላንት የተሻለውን ለዛሬው ይመርጣል፡፡ ይገባዋልም፡፡
የባሰበት ደም መጣጭ ርሃብተኛ አያ ጅቦ ሌቦ ቦጥቧጭ ፤ ከእጅ አይሻል ዶማ የሆነ የአቅም ውስንነት  ያለበት የሚሰራውን በውል የማይችል አስተዳዳሪ ከሆነ ተመስገን ሳይሆን የትላንቱን አምጡልኝ ያስብላል፡፡ገና ምን አየህ ተብሎ ለእንካ ቅመስ እጅጌ መሰብሰብም ነገ ያስተዛዝበናል፡፡

አዳዲሶች መሪዎቻችን ከቀደምቶቹ ስህተት ሊማሩ እና ሊያርሙ ይገባል እንጂ መሳ ለመሳ በፈሰሱበት ሊፈሱ አይገባም፡፡ የሱ ወይም የሷ ግዜ ተብሎ የምንዘክርላቸው አዲስ ሃሳብ አዲስ አሰራር አዲስ ለውጥ እንዲያሳዩን ከወዲሁ እጃችሁ ከምን ብለናል፡፡

ጥሎብን ይሁን ተጥሎብን ባላውቅም ዘመናችን ዝምታ ያይልበታል፡፡ ወንበር የሰጠናቸው ሰዎች ግን ንግግራችንን ብቻም ሳይሆን ዝምታችንም የሚገባቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡

                                              ሰላም!


ጋዜጠኛ ሃኒ ሰለሞን ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቀዋል፡፡ አሁን በሸገር ኤፍ.ኤም ሬዲዮ በጋዜጠኝነት በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሃሳብና አስተያየት ካለዎት በኢሜላቸው honeysolomon123@yahoo.com በፌስቡክ ገጻቸው https://www.facebook.com/honey.solomon.3 ሊያገኟቸው ይችላሉ፡፡

Wednesday, July 10, 2013

"ቦሌ እና ጉለሌ ወይም ሌላ…"

እህሳ እንዴት ሰነባብታችዋል?
የሰሞኑ ወሬ ሁሉ
ፖለቲካ ….ፖለቲካ…
ሹመት…ሹመት….
ሽረት….ሽረት….
ከንቲባ…ከንቲባ ምናምን ሆኗል፡፡ የሹም ሽሩን ነገር "ጉልቻ ቢለዋወጥ…" ነው፡፡ የቤት ምዝገባው ነገር አሁን ላይ ጋብ ያለ ይመስላል፡፡ ደግሞ ነሀሴ ገብቶ እነ 40/60 ሽር ጉድ እስኪሉብን፡፡
"መጀመሪያ የመቀመጫዬን አለች ዝንጀሮ" አሉ? እኔ አሁንም ቀልቤ ከቤቱ ላይ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ቤት ከግድግዳ እና ጣሪያም በላይ ነው፡፡ መቼም የኮንዶሚኒየም ቤት እጣ ተጀመረ ብሎ 80ውን ለመቅደድ ህሊናው የሚፈቅድለት ሰው ሲታይ እንዲህ ብሎ መናገር ያስደፍራል፡፡
ቤት የማይነጥፍ ላም ነውና ሁሉም ሊኖረው ቢኖረውም ለመጨመር ለመጨማመር ያስባል፡፡ ምክንያቱም ቤት ነው፡፡ ከተማዋ ደግሞ አዲስ አበባ…
በርግጥ የችግሩ ስፋት ምንም ያስኮናል፡፡
ቆየት ቢልም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ 5 ዓመት በፊት የተሰራን ጥናት ብነግራችሁ ጨዋታዬን ያሳምረዋል፡፡ በቤት ቁጥሩ ላይ መሻሻል ይኖራል ብለን ብናስብ እንኳ ሰውም የዚያኑ ያህል ተሰግስጓልና ችግሩ  ቢብስ እንጂ ያገግማል የሚል ሃሳብ መስጠት ይከብዳል፡፡
በአዲስ አበባ ከሚገኙ ቤቶች 84.4 በመቶ ያህሉ መኖሪያ ናቸው ቢሆንም ከቤት ፍላጎቱ አንጻር ይህ ቁጥር 60 በመቶ ገደማ እንኳ አይሸፍንም፡፡ በከተማዋ ካሉት መኖሪያ ቤቶች መጪውን 20 ዓመት ሊሸጋገሩ የሚችሉት ደግሞ 35 በመቶው ብቻ ናቸው፡፡
እነዚህ ቤቶች ቤት መባላቸው ብቻ ለኑሮ የተመቹ የሚለውን የሚወክል አይደለም፡፡ የማእከላዊ ስታትስቲክስ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በከተማዋ ከሚገኙ መኖሪያ ቤቶች 75 በመቶው መፀዳጃ ቤት እና 26 በመቶው ማድ ቤት የሌላቸው ናቸው፡፡ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ባለ አንድ ክፍል  ናቸው፡፡
ታሪክን የኋሊት
ቀድሞ አዲስ አበባ ስትቆረቆር የደጃዝማች ፤ የራስ እገሌ ሰፈር እየተባለ የጦር አለቆቹ በስራቸው ያሉትን እያስተዳደሩ ትኖር ነበር ይላሉ የታሪክ ሰዎች፡፡
ከዛማ ጣሊያን ገባ ፒያሳ እና ካዛንቺስ የመደብ ልዩነትን አመጡ፡፡ የሮም ሰዎች ካዛንችስን ለመኖሪያቸው ፒያሳን መገበያያቸው ሲያደርጉ መርካቶ…'ተራ' ተብለው ለተጠሩት አባት አያቶቻችን ለመገበያያነት  ተዘጋጀች፡፡
ጣሊያን ጥፋቷ ሳይበዛ ቶሎ ለቃ መውጣቷ እንዲሁም በቅኝ ግዛት አለመውደቃችን የነጭ የጥቁር ወይም በሃይማኖት ልዩነት የተከፋፈለ አኗኗር እንደሌላው የአፍሪቃ ሀገር ጎልቶ እንዳይወጣ ቢያደርግም በከተማችን እንዲህ አይነቱ የኑሮ መደብን መሰረት ያደረገ አከታተም ብቅ ካለ ሰነባብቷል፡፡
አሁን በአዲስ አበባ የሀብታምና የደሀ ሰፈር አለ፡፡ የተራራቀ የሀብት ልዩነትም እንዲሁ፡፡ በአዲስ አበባ ድሃው ህዝብ በቪዛ እንደሚሄድባቸው ሃገሮች ሩቅ የሚመስሉት ቢሄድም ባይተዋረኝነት እንዲሰማው የሚያደርጉ ሰፈሮች ፤ ሀብታሙ ደግሞ ቀልድ አዋቂ ነን የሚሉ ሙያተኞች ሲቀልድባቸው ከመስማት ውጭ በውል የት እንዳሉ እንኳ በርግጠኝነት የማያውቃቸው ሰፈሮች ተበራክተዋል፡፡
በሪል ስቴት መንደሮች የቤቱ ቀጥተኛ ነዋሪ ካልሆኑ ወይም ቀድሞ እኔጋ እሚመጣ እንግዳ አለ ብሎ ስምዎን ከዘቦቹ የሚያስመዘግብ ሰው ከሌለ በቀር እንዲሁ ዘው የማይባልባቸው በጥርብ ድንጋይ የታጠሩ አደገኛ በሚል የኤሌትሪክ ሽቦ የተከለሉ ግቢዎች ብዙ ናቸው፡፡ በዚህ አከባቢ መኖር ብቻ አይደለም እምጠይቀው ዘመድ አለኝ ማለት የኑሮ ደረጃዎን ከፍ ያደርጋል፡፡
ቀድሞ ሪል ስቴት እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ወይም የኮንደሚኒየም ቤቶች ጉዳይ ነበር ለችግሩ መባባስ እንደምክንያት የሚነሳው፡፡
አሁን ደግሞ 10/90 ፤ 20/80፤ 40/60፤ ……… ተጀምሯል፡፡ ይህ አዲስ የቤቶች ፕሮግራም ቀድሞ የታሰበ እና ዝግጅት ያልተደረገበት መሆኑን የሚያሳብቁ ችግሮችን ገና ካሁኑ ማግተልተል ጀምሯል፡፡ መሰንበት ደጉ ገና ደግሞ ያሳየናል፡፡
የከፍተኛ ሀብታም ሰፈር፣ የመካከለኛ ሀብታም ሰፈር፣ መካከለኛ፣ የድሃ እና የፍጹም ድሃ ሰፈር ብሎ መከፋፈሉ ከዚህ ሰፈር ነኝ ማለት የሚያፍሩ ልጆች እዚህ ሰፈር ዘመድ አለኝ ብለው የሚጠይቃቸው ስጋ የሌላቸው ነዋሪዎችን እንዳይወልድልን ነዋሪውን የማሰባጠሩ ጉዳይ ላይ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባ ነበር… ግን አልሆነም፡፡ እስካሁን ሲነገር የሰማነው የቦታ አደላደል ከፋፍለህ አሳድር አይነት ነው፡፡
10/90 የቤት ፕሮግራም በፍፁም ድህነት ስር ላሉ ዜጎች የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡ ፕሮግራሙ መታሰቡ ጎሽ የሚያስብል ነው፡፡ ግን ደግሞ ቤቱ የት ይገነባል? እነዚህን ሰዎች አንድ ቦታ ላይ አጉሮ ማኖርስ አዲስ አበባ ከሌሎች አቻ ከተሞቿ ትሻላለች ያስባላትን የስብጥር ኑሮ አያጠፋው ይሆን የሚለውን ጥያቄ ያመጣል፡፡
አሁን ላይ ምዝገባው በተጠናቀቀው 10/90 የተመዘገበው ሰው ቁጥር ከታሰበውም ቀድሞ ከተጀመሩት የቤቶች ግንባታም ያነሰ ነው፡፡ 187 ብር በወር ቆጥቤ መንግስቴ ለምንዱባን ብሎ እሚሰራው ቤት ከምኖር 274 ብር ቆጥቦ በ20/80 የአንድ መኝታ ቤት ባለቤት ለመሆን ከ900 ሺህ ሰው ውስጥ የተአምር እድል መጠበቅ እመርጣለሁ የሚል ይበዛል፡፡ አሊያም የሰዉ የኑሮ አቋም መንግስት አያውቀውም ማለት ያስችል ይሆና፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን በጥናት አልመጣም ያስብላል፡፡
ባለመካከለኛ ገቢው ባለ 20/80ው አንድ ላይ… ውጪ ቀመስ የሆነውን ዲያስፖራ እና ሀገር በቀሉን ባለ ገንዘብ አንድ መንደር ማጎሩ መዘዝ አለው ይላሉ የህብረተሰብ ሳይንስ ባለሙያዎች፡፡ አብሮ ካለመኖር ካለመተዋወቅ አለመተዛዘን አለመተሳሰብ በጠላትነት መተያየትን ያመጣል፡፡
ኢትዮጵያዊ ሲኖር የሌለው ባለው ይፅናናል፡፡ ሃብታሙም የተቸገረ መኖሩን ሲያውቅ ነው ተመስገን የሚለው፡፡
ድሃው ድርሽ የማይልባቸው ቢመጣ እንኳ ቀኑን ሙሉ ለባለጠጋው ጉልበቱን ሲሸጥ ውሎ የሚመለስባቸው ሰፈሮች በአንድ አንድ ሀገሮች አሉ ይባላል በአፍሪቃ፡፡
አዲስ አበባ የአፍሪቃም ነች ስንል ከደሃው እየነፈግናት አይደለም፡፡ አንተ የእንትን ሰፈር ልጅ ተብሎ የሚሰደብ፣ እኔ የዚህ ሰፈር ልጅ ነኝ እያለ ሌላው ቆዳውን የሚያዋድድባት ከተማ ልትሆን አይገባም፡፡
ቢታሰብበት አይበጅም?

ቸር ሰንብቱ!


ጋዜጠኛ ሃኒ ሰለሞን ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቀዋል፡፡ አሁን በሸገር ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጋዜጠኛ ናቸው፡፡ ሃሳብና አስተያየት ካለዎት በኢሜይላቸው honeysolomon123@yahoo.com በፌስቡክ ገጻቸው https://www.facebook.com/honey.solomon.3?fref=ts ሊያገኟቸው ይችላሉ፡፡

Wednesday, July 3, 2013

የቦሌው መንገድ - ላለው ይጨመርለታል

        ልማትን አጥብቆ የሚወደው ኢ-ቲቪያችን የቦሌን መንገድ አስመልክቶ አንድ የቢዝነስ ወሬ አቀረበ፡፡ ከመስቀል አደባባይ አውሮፕላን ማረፊያ (ቻይና አደባባይ መሠለኝ) ያለው መንገድ ስራ አልቆ ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ ውሏል አለ፡፡ እናም በመንገዱ ስራ ምክንያት ስራቸው ቀዝቅዞባቸው የነበሩት የንግድ ቤቶች አሁን ገበያው ድርላቶቸዋል ብሎም ጨመረ፡፡ አንዳንድ ገበያችን ከ 70 በመቶ ወደ 85 በመቶ ጨምሯል የሚሉ ጥናት ሳይሰሩ በመቶኛ መነጋገር የሚቀናቸውን ነጋዴዎችም አስተያየታቸውን ሰጡ ፡፡ አይ ጥሩ ነው እንኳንም ገበያችሁ ደራ ብለናችኋል፡፡ እነዛ የመንገዱ ስራ በተባለው ጊዜ ባያልቅ ቤተሰቤን ምን እመግባለሁ ብለው የሰጉ ነጋዴዎች ግን ንግዳቸውን ወደ ሌላ ሰፈር ቸኩለው አዛወሩ፡፡ ይሄው ዛሬ ሁለት ጉድጓድ ያላት አይጥ እንደሚባለው ሌላ ሰፈር መተዳደሪያ ሱቅ  የነበራቸው እና አንዳንድ ተስፋ በቀላሉ የማይቆርጡ ነጋዴዎች  ጥርሳቸውን ነክሰው ሰንብተው በዛሬው የደራ ገበያ ፈገግ ፈገግ ለማለት በቁ፡፡ ከዚህ ወጣ ያሉት የቦሌን መንገድ በእግርና በታክሲ የሚያቋርጡት መኪና የሌላቸው ዜጎች ግን ‹ስራው ተጠናቀቀ› የተባለው የቦሌ መንገድ ‹መቼ ተጠናቀቀና?› እያሉ ነው፡፡
ሚዲያዎች ማንን መሠረት አድርገው እንደሆነ እንጃ መንገዱ ተጠናቋል ብለው ይዘግቡ ከጀመሩ ሰነበቱ፡፡ ባለስልጣናትም ከሳምንታት በፊት በመንገዱ አካፋይ ላይ ለምለም ቅጠል ሻጥ ሻጥ ተደርጎላቸው ስራችንን ጨረስን መኪናም አስተላለፍን ብለው መጥተው መረቁት፡፡ እርግጥ ቅጠሎቹ አሁን ደርቀዋል፡፡ የአስፋልት ጥቁረት ምን መምሰል እንዳለበት የሚከራከሩ ባለመኪኖች ደግሞ ‹መንገዱ አላለቀም፡፡ ምክንያቱም ይሄ ጭቃ መሰሉ ነገር ጠፍቶ ድብን ያለ ጥቁር መሆን ስለሚገባው ገና አንድ ዙር አስፋልት ማልበስ እና ማስዋብ ይቀረዋል፡፡› እያሉ ነው፡፡ እነዚህ ባለመኪና የመንገዱ ተጠቃሚዎች በፊት በፊት ‹የቦሌ መንገድ የትራፊክ መጨናነቁ ገደለን መንገዱ ሰፋ ቢል ጥሩ ነበር፡፡› በሚል አብዝተው ሲማረሩ የኖሩና አሁን ፀሎታቸው ተሰምቶ የመንገዱ ስፋት የሚሆኑበት ጨንቋቸው በከፍተኛ ፍጥነት እየበረሩበት ያሉ ናቸው፡፡ ዛሬ ጠዋት አንዲት እናት ዕድሜአቸው በማይፈቅደው ሩጫ ነፍሴ አውጪኝ ብለው አስፋልት ከተሻገሩ በኋላ ቁና ቁና እየተነፈሱ እንዲህ አሉ ‹አሁንማ መንገዱም ሰፋላቸው!›፡፡ ባለመኪኖቹ በመንገድ ግንባታው ወቅት መንገድ ቀይረው፣ በመንገዱ መጣበብና መጨናነቅ ለረዥም ደቂቃዎች መኪናቸው ውስጥ ተቀምጠው ያሳልፉ የነበረበት ጊዜ ላይ ለመሳለቅ ይመስላል አሁን በአጭር ደቂቃ የፈለጉት ቦታ የመድረሳቸውን ተዓምር እያደናነቁ እንደጉድ ይበራሉ፡፡ እያደናነቁም ግን ‹መንገዱማ የማስዋብ ስራ›ይቀረዋል ይላሉ፡፡
የቦሌን መንገድ በስራም ሆነ በመተላለፍ አጋጣሚ የሚያዘወትራት እግረኛ በተመሳሳይ/በሚያስገርም ተቃርኖ ‹የቦሌ መንገድ አላለቀም!› ብሎ በድፍረት እየተናገረ ነው፡፡ ምክንያቱም የእግረኛ መረማመጃው ገና ኮረት እንደተከመረበት ነው፡፡ ጉድጓድም ሞልቶታል፡፡ እግረኞች የእግረኛ መንገዱ ገና በስራ እና በቁፋሮ ላይ በመሆኑ ከፈጣን መኪኖች ጋር ትከሻ ለትከሻ እየተጋፉ በመኪና መንገድ ላይ እየተጓዙ ነው፡፡ መሻገሪያ መራመጃ አጥቶ ሁለት ዓመት የተንገላታው እግረኛው ነው፡፡ ታክሲ የሚሳፈርበት እና የሚወርድበት ቦታ አልመች ብሎት ለልማቱ ሲባል ‹ቻለው› የተባለው እግረኛው ነው፡፡ አቧራ እና ጭቃ ተፈራርቆበት ለዓይንና ለባክቴሪያ ህመም እና የህክምና ወጪ የተዳረገው እግረኛው ነው፡፡ 3 ብር ከ70 ይከፍልበት ለነበረው መንገድ 8 ብር እየከፈለ የሄደው እግረኛው ነው፡፡ ለእግረኛው መንገዱ የሚጠናቀቀው ስቃዩ ሲጠናቀቅ ነው፡፡
አዲሱ የቦሌ መንገድ አምሮበታል፡፡ መኪና የሌለው ደሀ (እግረኛ)  አልይ ያለ ይመስላል፡፡ በየመሀሉ ለእግረኛ የሚሆን መቋረጫ እንዲኖር አልፈቀደም፡፡ ታክሲዎችም እዛም እዛም እየቆሙ እንዲጭኑና እንዲያራግፉ አይወድም፡፡ ስለዚህ እግረኛ ስሙም ከነመጠሪያ እግረኛ ነውና በእግሩ እንዲሄድ ተፈርዶበታል፡፡ ለምሳሌ ከፒያሳ ደንበል ህንፃ ድረስ በታክሲ መምጣት የሚፈልግ ሰው ቀደም አድርጎ ፍላሚንጎ ጋር ወርዶ በእግሩ እንዲሄድ ይጠየቃል፡፡ ባለታክሲዎቹ መንገዱ በሙሉ ‹ክልክል በክልክል› ሆነብን ብለው ያማርራሉ፡፡ ማውረድ ክልክል ነው፡፡ ተሳፋሪውም ታሪፉ እንኳን ቢቀነስልን ብለው ያሳቅላሉ፡፡ አንድ ወቅት ላይ የህዝብ ማመላለሻ ዋጋ ታሪፍ በመንግስት አባባል ‹ሲሻሻል› በህዝቡ አቀባበል ደግሞ ‹ሲጨምር› ይመለከተኛል ያለው የመንግስት አካል ህዝቡ በኪሎሜትር መክፈል ያለበትን ዋጋ በጋዜጣ አትሞት ነበር፡፡ ለአብነት ያህል በጋዜጣው ስሌት መሠረት ከፒያሳ ደንበል ሸዋ ዳቦ የሚወስደው የታክሲ ዋጋ 2 ብር ከ70 ሳንቲም ነው ብሎ አወጀ፡፡ ጋዜጣውን እማኝ አድርገው መክፈል ያለብን 2፤70 እንጂ 3፡70 አይደለም ብለው የተከራከሩ ተሳፋሪዎች ከታክሲ ሾፌሮች ግልምጫ ከረዳቶቸ ደግሞ እርግጫ (ቀረሽ) ምላሽ ሲደርስባቸው ብሶታቸውን ለሚመለከተው አምላክ ሰጥተውት ዝም አሉ፡፡ የቦሌው አዲሱ መንገድ ደሀውን ከሳንቲሙም፣ከጉልበቱም ከጊዜውም፣ በጥቅሉም ከልማቱም ያስተረፈለት የለም፡፡ ታዲያ መንገዱ ለደሀው እግረኛ ምኑ ነው? ለባለመኪና ፍጥነት ጨምሯል ለእግረኛው ስቃይ ጨምሯል፡፡ እንግልትም ምቾትም እንዴት ላለው ይጨመርለታል?


አንዳንድ ሀገራት ለህዝባቸውም ርካሽ የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፓርት ማቅረብ ሲታክታቸው ሰፋፊ መንገዶችን ይሠሩና ህዝባቸው መኪና እንዲገዛ ያበረታታሉ፡፡ በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ መንገዶች ለእግረኞች ሳይሆን ለባለመኪኖች እንዲመቹ ተደርገው እየሰፉ ነው፡፡ እግረኛው በእግሩ እና በታክሲ መሄድ አላዋጣው እንዲለውና የራሱን መኪና እንዲገዛ ከሆነ እሰየው፡፡ ሆኖም መኪና የገዙ ፣ለመግዛት ያሰቡ በአጠቃላይ የመግዛት አቅሙ ያላቸው ሰዎች መኪና ቀረጥ መቶ ሀምሳ እጥፍ መሆኑ የሚቀመስ አላደረገው እያሉ እያማረሩ ነው፡፡በዛ ላይ ገንዘቡስ ከየት ይመጣል? በሌላ በኩል ጠባብ መንገድና ከተማ እንዲሁም በርካታ ህዝብ ያላቸው ሀገሮች የመኪና ዋጋን ሳይሆን የመኪና ማቆሚያ ስፍራ በማሳጣትና ኪራዩንም በማስወደድ መኪና ለምኔ ብሎ እንዲተውና በተለይም በከተማ ባቡር እንዲጠቀም ያደርጉታል፡፡ አዲስ አበባ የከተማ የባቡር መንገድ እየተዘረጋ መሆኑ ህዝቡ መኪናም ባይኖረው የትራንስፓርት ፍላጎቱ እንዲሟላለት ይመስላል፡፡  የሚመስለንን ትተን እውነቱን እንጠይቅ፡፡ መንግስት ህዝቡ መኪና እንዲኖረው ፈልጓል ወይስ አልፈለገም? መንገድን ለማን ነው የሚሰራው? ለሞላው ለተደላደለው? ወይስ ላጣው ለነጣው? የቦሌው አዲሱ መንገድ በሁሉም የኢኮኖሚ ደረጃ ያሉትን ዜጎች እኩል ለማገልገል ታስቦ እንዳልተሰራ እያሳበቀ ነው፡፡ ለደሀው ተብሎ የለማው መንገድ የቱ ነው? ልማት ማለትስ ምን ማለት ነው?


ጸሃፌ ተውኔት መዓዛ ወርቁን በሸገር የአልጋ በአልጋ ተከታታይ ድራማና በህይወት መሰናዶ ድራማ ደራሲነታቸው እናስታውሳቸዋለን፡፡ አሁን እየታየ የሚገኝ ዝነኞቹ የተሰኘ ቴአትርም አላቸው፡፡ አስተያየት ካላችሁ በፌስቡክ አድራሻቸው በኩል በhttps://www.facebook.com/meaza.worku.39 ሊያገኙዋቸው ይችላሉ፡፡