ባለፉት
ሁለት ሳምንታት የሃገራችን ቋንቋዎች በተለይም አማርኛ ለቀጣይ ዘመን የሚሆነውን ዝግጅት ከአሁኑ መጀመር እንዳለበት ሳወራችሁ ቆይቻለሁ፡፡
ይህንንም የሚረዳ አንድ አይነት እንቅስቃሴ ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅትም እያደረግን ነው፡፡ አሁንም ይህንን ሃሳብ ለማገዝ የሚፈልግ
በኢሜል አድራሻዬ feruzj30@gmail.com ይላክልኝ፡፡ ጽሁፉን አንብባችሁ የተቻላችሁን ለማድረግ ቃል የገባችሁልኝን
ኢትዮጵያውያን አመሰግናለሁ፡፡ በተለይም አቶ ሞረሽ ሻሎምን ከደቡብ ኮሪያ፣ የኢንተርኔት አጠቃቀም መመሪያ በአማርኛ የተሰኘውን መጽኃፍ
ተባባሪ ደራሲ አቶ ወንደሰን አሰፋ፣ የሶፍትዌር ኢንጂነሩን አቶ ዮናስንና ለኖኪያ ስልኮች የሚሆን የአማርኛ ሶፍትዌር የሰሩት አቶ
ነቢዩን በጣም ላመሰግን እወዳለሁ፡፡
የአማርኛና
ሌሎች ሃገራችን ቋንቋዎች ለ21ኛው ክፍለዘመን የበቁ ማድረግ የሚጀምረው ቋንቋዎቹ በመጀመሪያ ደረጃ በዚህ ዲጂታል ኣለም ውስጥ ያላቸውን
ቦታ በማሳደግ ይሆናል፡፡ ለሺ ዓመታ ቆዩ ቋንቋዎች በሶስት ትውልድ ጊዜ ለመጥፋት ሲቃረቡ አይተናልና፡፡ ወደ ቤተመጻህፍት መሄድ ሳያስፈልግ፣ በጣም አዲስና ወዲያው ወዲው የሚታደስ
የእውቀት ቋት ቢኖርና ማንም ሰው ገብቶ ሊያገኝው ቢችል ሊፈጠር የሚችለውን የእውቀት ፍንዳታ ማሰብ ቀላል ነው፡፡ በኢኮኖሚ በለጸገ፣
በዲሞክራሲ ታነጸና ተራማጅ ሆነ ማህበረሰብ ለመፍጠር መቼም እንደ ትምህርትና እውቀት ሚሆን ነገር የለም፡፡ቤትምህርት ቤቱ ሚገኝ
በስርዓት የተዋቀረ ትምህርት ብቻ ደግሞ ይህንን መሰለ ለውጥ ሊያስከትል አይችልም፡፡ በመንግስት መዝገብ ቤቶች፣ በቤተ መዘክርና
ቤተ መጻህፍት፣ በሚዩዚሞች፣ በየቤቱ ያለና በሰው ዘንድ የሚገኝ እውቀት የሌለው ካለው እንዲያገኝ፣ እውቀት ለተወሰኑ ብቻ የተሰጠ፣ የታደሉት ብቻ የሚጠቀሙበት ሃብት መሆኑ እንዲያበቃ መሆን ይገባዋል፡፡ ይህ
ሁሉ መረጃ ከያለበት ተሰብስቦ ሁሉም በቀላሉ ሊያገኘው በሚችል ቦታ መቀመጥ አለበት፡፡ እውቀት ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ መብቶች አንዱ
ነው፡፡ ቤንሻንጉል ገጠር ያለ፣ አፋር ከግመሎቹ ጋር የሚውልና አዲስ አበባ የሚኖር እኩል ተፈጥሯዊ የእውቀት ጥማት አላቸው፡፡ በመሆኑም እድሉ ያለን ዜጎች፣
ሃላፊነቱን የሰጠነው መንግስትና ሌሎች ሚመለከታቸው ወገኖች ግዴታችንን መወጣት አለብን፡፡
ቢሮክራሲ
ባለተጫነው ሁኔታ ሰዎች ባሉበት ሃገር ሆነው ለዚህ የእውቀት ቋት ማበርከት ቢችሉ፣ ይህንን የሚያስተባብረውም አካል የአርትኦት ስራውን ከቋንቋ፣ ከቁጥሮችና ከማጣቀሻዎች አንጻር ቢያከናውን፣ የአይቲ ባለሙያዎች
በተለያዩ መልኩ በስልክ፣ በኮምፒውተር ወይንም በማንኛውም ኤሌክትሮኒካዊ የመገናኛ ዘዴዎች ሁሉም ባመቸው ወቅትና ቦታ እንዲታይና እንዲገኝ ቢደረግ፣
ተጠቃሚውም ከምንም አይነት ክፍያ ነጻ በሆነ ሁኔታ አገልግሎቱን ቢያገኝ የፕሮጀክቱ ዋና መነሻ ምክንያቶች ናቸው፡፡ከአማርኛም በተጨማሪ
በሌሎች የሃገራችን ቋንቋዎች ይህ የእውቀት ቋትን ማግኘት ቢቻል ቅድም ያወራናችን እውቀት የሁሉም ዜጋ ተፈጥሯዊም፣ ህጋዊም እንዲሁም
ሞራላዊም መብት ነው ያልኩትን ማስፈጸም ይቻላል፡፡ ይህንን ሁሉ ለማድረግ ገንዘቡም፣ እውቀቱም ፍላጎቱም በኛው በዚህች ሃገር ዜጎች
ይገኛል፡፡ ምናልባት የፈቃደኝነት እና የግንዛቤ ማጣት ካልሆነ በቀር፡፡ መንግስትም ቢሆን የዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም ኢትዮጵያ
ለማኖር ባህልን፣ ቋንቋንና ታሪክን ዘመን እንዲሻገሩ ማድረግ ሃፊነት አለበት፡፡ የክፍለ ሃገር ልጅ እንደመሆኔ በተለይ በቤተ መጻህፍትና
ቤተ መዘክር የሚገኙ መረጃዎችን ለማግኘት አዲስ አበባ መኖር የግድ መሆኑን ሳስበው ያሳዝነኛል፡፡ የተከማቸው መጽሃፍ፣ ማይክሮ ፊልምና
ሌላውም ሁሉ አዲስ አበቤዎች መሆኑ ይገርመኛል፡፡ ነገር ግን በየደረስኩበት ሁሉ ይህንን የሃገሬን እውቀት ባገኝ ለኔ በግሌ ከማገኘው
ጥቅም በለጠ ለሃገር ይሰጣል፡፡
ጸሃፊው ፌሩዝ ጀማል በሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 ሬዲዮ በ IT, ድምጽ ላይብረሪና ፕሮግራም ትራፊክ ሃላፊነት ይሰራሉ፡፡ ጸሃፊውን ለማግኘት በፌስ ቡክ ገጻቸው https://www.facebook.com/feraj?ref=tn_tnmn በኢሜላቸው feruzj30@gmail.com መጠቀም ይቻላል፡፡